ፕሬዝደንት ፑቲን ሩሲያ መደበኛ የሚሳይል ጥቃት የሚያጋጥማት ከሆነ የኑክሌር መሳሪያዎች ልትጠቀም እንደምትችል ተናግረዋል
ሩሲያ ለረጅም ጊዜ ስትጠቀምበት የነበረውን የኑክሌር ፖሊሲ መቀየሯን አስታውቃለች።
ክሬሚሊን ከትናንት በስትያ እንዳስታወቀው ሩሲያ የኑክሌር ኃይል አጠቃቃም ፖሊሲዋን የቀየረችው ምዕራባውያን በዩክሬን ጦርነት የሚሳተፉ ከሆነ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ለማስጠንቀቅ ነው።
ፕሬዝደንት ፑቲን ሩሲያ መደበኛ የሚሳይል ጥቃት የሚያጋጥማት ከሆነ የኑክሌር መሳሪያዎች ልትጠቀም እንደምትችል ተናግረዋል። ሞስኮ የኑክሌር ጦር መሳሪያ በታጣቁ ኃይሎች ድጋፍ የሚደርስባትን ጥቃት ጥምር ጥቃት አድርጋ ትቆጥረዋለች።
የሞስኮ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ፖሊሲ የመቀየር ውሳኔ፣ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይል ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንፍቀድላት ወይስ ይቅርብን በሚል በአሜሪካ እና በእንግሊዝ ለሚካሄዱ ውይይት መልስ የሰጠ ነው ተብሏል።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ የኑክሌር አጠቃቀም መመሪያው ማስተካከያ ተደርጎበታል ብለዋል። ማስተካከያው ለምዕራባውያን ማስጠንቀቂያ እንደሆነ የተጠየቁት ፔስኮቭ " ይህ ትክክለኛ ማስጠንቀቂያ መሆን አለበት" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"ይህ እነዚህ ሀገራት በኑክሌር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች በሀገራችን ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ከሆነ የከፋ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው ለማስጠንቀቅ ነው" ብለዋል ፔስኮቭ።
ኑክሌር የታጠቁትን ጨምሮ ምዕራባውያን በዩክሬን ጦርነት የሚያደርጉት ቀጥተኛ ተሳትፎ አለምን ወደአልተጠበቀ ፍጥጫ ውስጥ ሊያስገባት ነው ሲሉ ተናግረዋል ፔስኮቭ።
የስራ ዘመናቸው የተጠናቀቀው የኔቶ ዋና ጸኃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ሞስኮ ጥምረቱን ለማስፈራራት እየሞከረች ነው ብለዋል። "የሩሲያ የኑክሌር ማስፈራሪያ አደገኛ እና ግድሌሽነትን የሚያሳይ ነው" ያሉት ዋና ጸኃፊው "ሩሲያ እየሰራች ያለውን በቅርበት እየተከታተልነው ነው" ብለዋል።
በ2020 የተዘጋጀው እና የፕሬዝደንት ፑቲን ፊርማ ያረፈበት የአሁኑ የሩሲያ ኑክሌር መመሪያ፣ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም የምትችለው ጠላት የኑክሌር ጥቃት ሲከፍትባት ወይም ህልውናዋን አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል መደበኛ ጦርነት ሲገጥማት እንደሆነ ይገልጻል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የፑንን አስተያየት "ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው" ብለውታል።