ዩክሬን የሩሲያን ቦምብ ጣይ አውሮፕላን መትታ መጣሏን አስታወቀች
ሩሲያ በበኩሏ በምስራቃዊ ዩክሬን በዶኔስክ ግዛት ተጨማሪ መንደሮችን መቆጣጠሯን ገልጻለች
ኬቭ የሞስኮን ግስጋሴ ለማስቆም አጋሮቿ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን እንድትጠቀም እንዲፈቅዱላት እየወተወተች ነው
ዩክሬን የሩሲያን የጦር አውሮፕላን መትታ መጣሏን አስታወቀች።
ቦምብ ጣይ አውሮፕላኑ በዶኔስክ ግዛት ኮስቲያንቲኒቭካ ከተማ ነው ተመትቶ የወደቀው።
የዩክሬኑ መገናኛ ብዙሃን ሱስፒልን አውሮፕላኑ ተመትቶ ሲወድቅ ያረፈበትን መኖሪያ ቤት በእሳት ማያያዙን ዘግቧል። የአውሮፕላኑን ቁርጥራጮች የሚያሳዩ ምስሎችንም ለቋል።
ሩሲያ በበኩሏ በምስራቃዊ ዩክሬን ዶኔስክ ግዛት ተጨማሪ መንደር መቆጣጠሯን ገልጻለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ዝሄላን ድሩሄ የተባለችው መንደር በሞስኮ እጅ መግባቷን ይፋ ማድረጉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ሩሲያ ከአራት ቀናት በፊት ከዝሄላን ድሩሄ በ33 ኪሎሜትር ርቀት የምትገኘውን ቩሄልዳር ከተማ ከሁለት አመት ብርቱ ጦርነት በኋላ መቆጣጠሯ የሚታወስ ነው።
የቩሄልዳር ከተማ በሩሲያ መያዝ ኬቭ የመከላከል አቅሟ እጅጉን እየተዳከመ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተዘግቧል።
ዩክሬን ከምዕራባውያን የተሰጧትን ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች የሩሲያን ግዛት ዘልቀው በመግባት ጥቃት ለማድረስ እንዲውሉ መወትወቷን ብትቀጥልም እስካሁን ምላሽ አላገኘችም።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም ይህንኑ ጥያቄያቸውን ከስድስት ቀናት በኋላ በሚደረገው የ”ራመስቴን ቡድን” ስብሰባ ላይ እንደሚያነሱት በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ለኬቭ የጦር መሳሪያ ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራትን በአባልነት የያዘው ”ራመስቴን ቡድን” 25ኛውን ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሪዎች ደረጃ እንደሚያካሂድም ነው የተነገረው።
32ቱንም የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና 25 ሌሎች ሀገራትን በድምሩ 57 ሀገራትን ያካተተው ቡድን በሚያደርገው ምክክር ዜለንስኪ የኬቭን “የድል እቅድ” እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
“የድል እቅዱ” ዝርዝር ጉዳዮች እስካሁን በይፋ ባይወጡም ዩክሬንን የኔቶ አባል የማድረግና ሩሲያን በረጅም ርቀት ሚሳኤል ማጥቃት ተካተውበታል ነው የተባለው።