በሶማሊያ በተፈጸሙ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች 15 ሰዎች ተገደሉ
የሁለት የሀገሪቱን ባለስልጣናት መኖሪያ ቤቶች ኢላማ ያደረጉት የቦምብ ጥቃቶች በርካቶችን ማቁሰላቸው ተነግሯል
ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ ባይኖርም አልሸባብ ሳይፈጽመው እንዳልቀረ ተገምቷል
በሶማሊያ በተፈጸሙ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች 15 ሰዎች ተገደሉ።
በሂራን ክልል ማሃስ በተባለ አካባቢ በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸሙት ጥቃቶች የሁለት የሀገሪቱን ባለስልጣናት መኖሪያ ቤቶች ኢላማ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ሙሃመድ አቡ በከር ጃፈር እና ሙሃመድ ሃላኒ የተባሉት ባለስልጣናት በቤታቸው ውስጥ ባለመኖራቸው ከቦምብ ጥቃቶቹ ተርፈዋል።
የግለሰቦቹ መኖሪያ ቤቶች የሶማሊያ ጦር የሰፈረበት እና አልሸባብን የሚዋጉ ታጣቂዎች መገኛ ስፍራ ሲሆን በርካታ ሱቆችና ምግብ ቤቶች ይገኙበታል።
ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ ባይኖርም አልሸባብ ሳይፈጽመው እንዳልቀረ ተገምቷል።
የማሃስ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ኦስማን ኑር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት ማብራሪያ ፥
“የተሸነፉት አሸባሪ ሃይሎች ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በተሸከርካሪዎች ላይ በተገጠሙ ቦምቦች ፈጽመዋል” ሲሉ አልሸባብን ተጠያቂ አድርገዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ ዳግም ወደ ስልጣን እንደመጡ በአልሸባብ ላይ ጦርነት ማወጃቸው ይታወሳል።
ዛሬ ጥቃት በተፈጸመበት ማዕከላዊ ሶማሊያ የሚገኙት “ማካዊስሊ” የሚል ስያሜ ያላቸው ታጣቂዎችም በሽብር ቡድኑ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ መቀላቀላቸው አይዘነጋም።
የሶማሊያ ጦር እና የ“ማካዊስሊ” ታጣቂዎች ከሃምሌ ወትር 2022 ጀምሮ በከፈቱት ዘመቻም በርካታ ከተሞችን ከአልሸባብ ነጻ ማውጣታቸው ነው የተነገረው።
በዚህ ዘመቻም የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና አሜሪካ (በአየር ድብደባ) መሳተፋቸውን ነው ሬውተርስ ያወሳው።
አልሸባብ ለዚህ አጻፋም በጥቅምት 29 2022 በሞቃዲሾ ለ121 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ጨምሮ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ፈጽሟል።
በሶማሊያ ጦር እና በጸረ አልሸባብ ታጣቂዎች ከፍተኛ እርምጃ እየተወሰደበት በደቡባዊ ሶማሊያ በተወሰኑ ገጠራማ አካባቢዎች ተደብቋል ነው የተባለው።
የሽብር ቡድኑ ዛሬ በሂራን ክልል በደረሰው ጥቃትም እጁ እንዳለበት ቢታመንም እስካሁን ሃላፊነቱን አልወሰደም።