የአሜሪካ ጦር በፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ጥበቃ ላይ ሊሰማራ ነው
ጦሩ የሚሰማራው ለፕሬዝዳንቶች ጥበቃ የሚያደርገውን የደህንነት ተቋም (ሲክሪት ሰርቪስ) ለማገዝ ነው
በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ከተቃጣ በኋላ ሌሎች ጥቃቶች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል
የአሜሪካ ጦር የ2024 ምርጫ ላይ የሚሳተፉ እጩዎችን ለመጠበቅ ሊሰማራ መሆኑን ፔንታጎን አስታውቋል፡፡
ጦሩ ለፕሬዝዳንቶች እና ለምክትል ፕሬዝዳንቶች ጥበቃ የሚያደርገውን የአሜሪካ የደህንነት ተቋም ወይም “ሲክሪት ሰርቪስን” ለማገዝ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ነው የተነገረው፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን የሀገሪቱ ሰሜን እዝ ለደህንነት ተቋሙ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ስለሚችልባቸው ቁሳቁሶች እና የሰው ሀይልን የተመለከተ እቅድ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሳብሪና ሲንግ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት እጩዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች የትራንስፖርት፣ የሎጂስቲክ እና የኮምኒኬሽን አገልግሎት ላይ የመከላከያ ሚንስትሩ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ቃል አቀባይዋ የገለጹት፡፡
በሀምሌ ወር በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉን ተከትሎ ሌሎች ጥቃቶች በፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ላይ ሊሰነዘር እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት በሀገሪቱ አንዣቧል፡፡
ቶማስ ማቲው የተባለ የ20 አመት ወጣት ትራምፕ ንግግር ከሚያደርጉበት ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ በተኮሰው ጥይት ፕሬዝዳንቱ መጠነኛ ጉዳት ሲደርስባቸው የአንድ ታዳሚ ህይወት አልፏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ በእጩዎች ላይ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች እየተሰነዘሩ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የትራምፕን የግድያ ሙከራ ቀድሞ መከላከል አልቻለም የተባለው የሀገሪቱ የደህንነት ተቋም ከፍተኛ ወቀሳዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡
አለፍ ሲልም የተቋሙ ዳይሬክተር “በቸልተኝነት” ጥፋተኛ ተብለው የግድያ ሙከራውን ቀድሞ ማስቆም ለምን እንዳልተቻለ በኮንግረሱ ተጠያቂ ተደርገው ከስራቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ እጩዎች ከግዛት ግዛት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመጨመሩ ተመሳሳይ የግድያ ሙከራ እንዳይደረግ ነው መከላከያው ድጋፍ አደርጋለሁ ያለው፡፡
የአሜሪካ ጦር እጩዎቹን ለመጠበቅ ምን ያህል የሰው ሀይል እንደሚያሰማራ እና በምን አይነት መንገድ ጥበቃ እንደሚያደርግ ይፋ ባያደርግም፤ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ድረስ “ከሰክሪት ሰርቪስ” ጋር በትብብር ለመስራት እቅድ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡