የአሜሪካ የሚስጥራዊ ደህንነት ኃላፊ ስልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ
አባላቱ ኃላፊዋ ከስልጣናቸው እንዲለቁ የጠየቁት በትራምፕ ላይ ከተፈጸመው የግድያ ሙከራ ጋር በተያያዘ ነው
የዲሞክራት እና ሪፐብሊካን የተወካዮች ምክርቤት አባላት የአሜሪካ ሚስጥራዊ ደህንነት ኃላፊ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል
የአሜሪካ የሚስጥራዊ ደህንነት(ሰክሬት ሰርቪስ) ኃላፊ ስልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ።
የዲሞክራት እና ሪፐብሊካን የተወካዮች ምክርቤት አባላት የአሜሪካ ሚስጥራዊ ደህንነት ኃላፊ ክምብርሊ ቻትል ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።
አባላቱ ኃላፊዋ ከስልጣናቸው እንዲለቁ የጠየቁት የሪፑብሊካኑ ፕሬዝደንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ እንዲፈጸም ምክንያት ለሆነው የጸጥታ ክፍተት ተጠያቂ በማድረግ ነው። ነገርግን ኃላፊዋ ጥሪውን ውድቅ ከማድረጋቸው ባሻገር ተጨማሪ ማብራሪያም ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።
በብዙ ጉዳዮች የተለያየ አቋም በማንጸባረቅ የሚታወቁት የተወካዮች ምክር ቤት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ የሪፐብሊካን ሊቀመንበር ጄምስ ኮመር እና የዲሞክራቱ ከፍተኛ ፖለቲከኛ ጄሚ ራስኪን ቻትል ከስልጣን ይነሱ የሚል ተመሳሳይ ድምጽ አሰምተዋል።
"ይህ ኮሚቴ የሚታወቀው የተለያየ አቋም በመያዝ ነው፣ ዛሬ ግን ወደ አንድ መጥተናል" ሲሉ ኮመር ለቻትል ነግረዋቸዋል።
"በአንቺ አመራርነት እምነት የለንም"
ራስኪን በበኩላቸው ቻትል "በሀገራችን ታሪክ የኮንግረሱን እምነት አጥታለች፤ ስለሆነም በፍጥነት ከዚህ በላይ መሄድ አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።
ቻትል 4 1/2 ሰአት በፈጀው የኮንግረስ ቆይታቸው በፈረንጆቹ ሐምሌ 13 የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በ1981 በቀድሞው ፕሬዝደንት ሮናልድ ሪገን ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በማወዳደር "በአስር አመታት ውስጥ ጉልህ የሚባል የጸጥታ ክፍተት ነው"ሲሉ ገልጸውታል።
ነገርግን ከኃላፊነት እንዲነሱ የበረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉትም፤ "በዚህ ሰአት ሚስጥራዊ የደህንነት አገልግሎቱን ለመምራት የተሻልኩ ሰው ነኝ ብየ አስባለሁ" ሲሉም አክለዋል።
ቻትል ትራምፕ በፔንስልቬንያ የምርጫ ቅስቀሳው እያደረጉ በነበረበት ወቅት ስለተደረገባቸው የግድያ መከራ ጋር በተያያዘ በተወካዮች ፊት ቀርበው ሲያስረዱ የትናንትናው የመጀመሪያቸው ነው።
ትራምፕ በጆሯቸው ላይ የመቁሰል አደጋ ሲያጋጥማቸው፣ ከድጋፍ ሰልፉ ተሳታፋዎች ደግሞ አንድ መገደሉ እና ሌላ አንድ መቁሰሉ ይታወሳል።
ግድያውን በማድረስ የተጠረጠረው የ20 አመቱ ቶማስ ክሩክስ በጸጥታ አካላት ተገድሏል። ተኩስ የከተፈው ወጣት አላማ ምን እንደሆነ አልታወቀም።