አሜሪካዊያን ሙስሊሞች በቀጣዩ ምርጫ ፕሬዝዳንት ባይደንን እንደማይመርጡ ገለጹ
ፕሬዝዳንት ባይደን የእስራኤልን ድርጊት ካላስቆሙ በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደማይመርጣቸው ገልጸዋል
ፕሬዝዳንት ባይደን እና አስተዳድራቸው በአሜሪካ ጸረ እስልምና የሆኑ ድርጊቶችን እያስቆመ አይደለም ተብሏል
አሜሪካዊያን ሙስሊሞች በቀጣዩ ምርጫ ፕሬዝዳንት ባይደንን እንደማይመርጡ ገለጹ።
ሐማስ ያልተጠበቀ ጥቃት በእስራኤል ላይ ማድረሱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት 33ኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን እስራኤል በአየር እና በምድር ላይ ጥቃቷን በጋዛ እያካሄደች ትገኛለች፡፡
የአሜሪካ እስልምና ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ "ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን የተቀናጀ ጥቃት ካላስቆሙ በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ድምጻችንን አያገኙም" ብሏል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኒሀድ አዋድ እንዳሉት "ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ ተመስርተን የጋዛን ቀውስ ማስቆም ካልቻልክ እኛም ድምጻችንን አንሰጥህም" ብለን ነግረነዋል ብለዋል።
ኒሀድ አዋድ አክለውም ፕሬዝዳንት ባይደን አሜሪካዊ ሙስሊሞችን ከድቷል ያሉ ሲሆን የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲከሰትም ዝም ብሏል ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካ ለእስራኤል በቀጥታ በምታደርገው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እስራኤል ፍልስጤማዊያን ላይ የከፋ ስቃይ እያደረሰች ነው የሚሉት ኒሀድ ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካዊያንን ገንዘብ ለእስራኤል መስጠቱን እንዲያቆሙም ጠይቀዋል።
በአሜሪካ ጸረ እስልምና እምነት የሆኑ አግላይ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነውም የተባለ ሲሆን ፕሬዝዳንት ባይደን እና አስተዳደራቸውም ይህን ማስቆም እንዳልቻለም ተገልጿል።
በመሆኑም የአሜሪካ እስልምና ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ባይደንን እና ፓርቲያቸውን በቀጣዩ ምርጫ ወቅት በድምጹ እንደሚቀጣ ተገልጿል
ፕሬዝዳንት ባይደን በበኩላቸው "በጋዛ የተኩስ አቁም ማድረግ የማይታሰብ ነው" ያሉ ሲሆን በእስራኤል ጦር የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር 11 ሺህ እንደደረሰ ተገልጿል።
በእስራኤል ጦር ከተገደሉ ፍልስጤማዊያን ውስጥ 7ሺህ 300 ያህሉ ሴቶች እና ህጻናት ናቸውም ተብሏል።