በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች የጥቃት ኢላማ መደረጋቸው ተገለጸ
ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ 40 የድሮን ጥቃቶች በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ተሰንዝሯል
አሜሪካ በቀጥታ ለእስራኤል መወገኗን ተከትሎ ወታደሮቿ የጥቃቱ ኢላማ እንደተደረጉ ተገልጿል
በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች የጥቃት ኢላማ መደረጋቸው ተገለጸ፡፡
ሐማስ ያልተጠበቀ ጥቃት በእስራኤል ላይ ማድረሱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት 32ኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን እስራኤል በአየር እና በምድር ላይ ጥቃቷን በጋዛ እያካሄደች ትገኛለች፡፡
አሜሪካ በዚህ ጦርነት ዙሪያ ለእስራኤል መወገኗን እና ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ ኢራንን ጨምሮ በርካቶች ዋሸንግተንን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡
አሜሪካ በጦርነቱ ጣልቃ ከገባች ጦርነቱ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሊስፋፋ ይችላል፣ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የአሜሪካ ጦርም ጥቃት ሊደርስበት ይችላል በሚል ኢራን፣ ሂዝቦላህ እና የየመን አማጺዎች አስጠንቅቀው ነበር፡፡
በሶሪያ እና ኢራቅ ያለው የአሜሪካ ጦር ባለፉት 30 ቀናት 40 የድሮን ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች እንዳሏት የተገለጸ ሲሆን በኢራን ይደገፋሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ታጣቂዎች ጥቃት በመሰንዘር ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን ወደ እስራኤል ተኩሶ ነበር የተባለ ሲሆን በሜድትራኒያን ባህር ላይ የሰፈረው የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን አክሽፏል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች ጥቃት ሊሰነዘርብን ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ መውደቃቸው የተገለጸ ሲሆን የውጭ ጉዳየ ሚኒስር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኢራቅ አምርተው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥቃቱን እንዲያስቆሙ መጠየቃቸውም ተገልጿል፡፡
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ሱዳኒ የኢራቅ ታጣቂዎችን የመቆጣጠር አቅም የላቸውም የተባለ ሲሆን ወደ ኢራን አምርተው ታጣቂዎቹ በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እንዲያስቆሙላቸው መጠየቃቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል ከሃማስ ጋር እያደረገችው ያለው ጦርነት ከ51 ቢሊየን ዶላር በላይ ያስወጣታል ተባለ
ኢራን በበኩሏ ታጣቂዎቹ የሚንቀሳቀሱት በኢራቅ እንጂ በእኔ ግዛት አይደለም ጥቃቱን ማቆም የሚችሉት ራሳቸው ታጣቂዎቹ ናቸው ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው ሂዝቦላህ በበኩሉ እስራኤልን እያገዘች ዳር መቆም እንደማትችል እና ከአደጋ ነጻ ልትሆን አትችልም ብሏል፡፡
በእስራኤል እና አሜሪካ ላይ ጥቃት እንደሚከፍት የሚገልጸው ሂዝቦላህ የዋሸንግተን የጦር መርከቦችን ማጥቃት የሚችል ሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል መታጠቁ ተገልጿል፡፡
የእስራኤል -ፍልስጤም ጦርነት ከተጀመረ 33ኛ ቀኑ ላይ ሲሆን እስካሁን በእስራኤል ጦር የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር ከ11 ሺህ ገደማ የደረሰ ሲሆን በየዕለቱም 150 ህጻናት እየተገደሉ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላንን መትቶ መጣሉን የገለጸ ሲሆን አሜሪካ ለእስራኤል ድጋፍ ማድረጓን እንድታቆምም አስጠንቅቋል፡፡