አውሮፕላኑ የተመታው በራሷ የአሜሪካ ባህር ሀይል ጦር እንደሆነ ተገልጿል
አሜሪካ የጦር አውሮፕላኗ በየመን ተልዕኮ ላይ እያለ መመታቱን ገለጸች፡፡
የፍልስጤሙ ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ካደረሰ በኋላ እና እስራኤል የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በመካከለኛው ምስራቅ አለመረጋጋት አይሏል፡፡
በተለይም የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን ከሐማስ ጎን ነኝ ማለቱን ተከትሎ በቀይ ባህር እና አካባቢው ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን በመምታት ላይ ነው፡፡
አሜሪካ የሁቲን እንቅስቃሴ ለማስቆም በሰነዓ እና ሆዴዳህ ወደቦች ላይ በተደጋጋሚ የአየር ላይ ጥቃቶችን ስታደርስ ቆይታለች፡፡
በትናንትናው ዕለትም በሁቲ አማጹ ቡድን ይዞታዎች ናቸው በተባሉ ቦታዎች ላይ ድብደባ እያደረገች እያለ የጦር አውሮፕላኗ መመታቱን አስታውቃለች፡፡
የጦር አውሮፕላኑ አብራሪዎችን ህይወት መታደጉ የተገለጸ ሲሆን አንዱ አብራሪ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበታልም ተብሏል፡፡
አሜሪካ በሁቲ አማጺ ቡድን ይዞታዎች ላይ የአየር እና ባህር ሀይሎች ተቀናጅተው ሲደበድቡ ነበር የተባለ ሲሆን የጦር አውሮፕላኑ በስፍራው ባለው ሀሪ ትሩማ የተሰኘው የባህር ሀይል መርከብ አቅራቢያ ሲበር በስህተት እንደመታ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የአሜሪካ ጦር የሁቲ ቁልፍ ይዞታዎች እና የጦር መሳሪያ መጋዝኖች ላይ የተሳካ ድብደባ ተፈጽሟል፡፡
ከሐማስ ጎን ነኝ የሚለው ሁቲ ቡድን ከዚህ በፊት ሁለት መርከቦች ላይ ባደረሰው ጥቃት የሰመጡ ሲሆን የቀይ ባህር ንግድም ተስተጓጉሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በእስራኤል ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ያደረሰ ሲሆን በትናንታነው ዕለትም ቴልአቪቭን በባሊስቲክ ሚሳኤል መምታቱን አስታውቋል፡፡
እስራኤል በበኩሏ የሁቲ አማጺ የተኮሰውን ሚሳኤል ማክሸፍ እንዳልቻለች በጥቃቱም ከ20 በላይ ዜጎቿ ቀላል እና መካከለኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብላለች፡፡