ታይዋንን ሽፋን ያደረገው የዋሽንግተን-ቤጂነግ ፍጥጫ አሁንም እንደቀጠለ ነው
አሜሪካ ለታይዋን የምታደረገውን ወታደራዊ እርዳታ ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ የመከላከያ ህግ ማውጣቷ ቻይናን ማስቆጣቱ ተገለጸ፡፡
ቤጂንግ የአሜሪካ ውሳኔ “በታይዋን የባህር ዳርቻ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ድንጋጌዎች” የያዘ ነው ስትልም አውግዛለች፡፡
በተቃራኒ ታይዋን በአዲሱ የአሜሪካ የመከላከያ እርምጃ መደሰቷን ሮይተርስ ዘገቧል፡፡
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር፤ አዲሱ የመከላከያ ህግ ዋሽንግተን ለአሜሪካ-ታይዋን ግንኙነት መጠናከርና ለታይፔ ደህንነት የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብሏል፡፡
በታይዋን ላይ ለሚቃጣ ማንኛውም ጥቃት ካለ ከታይዋን ጎን ነኝ የምትለው አሜሪካ ለታይዋን አስፈላጊ የሚባለውን ድጋፍ ስታደርግ እንደቆየች የሚታወቅ ነው፡፡
በተለይም ከወራት በፊት የተደረገውን የፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ተከትሎ ፤ ቻይና በታይዋን ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች በሚል በምስራቅ ታይዋን አከባቢ ከፍተኛ ውጥረት እንደነገሰ የሚታወቅ ነው።
ለዚህም በታይዋን ባህር ዳርቻ እና በአካባቢው ያለውን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ አሜሪካ ወታደራዊ ልምምዶች ማድረግን ጨምሮ "ተጨባጭ እርምጃዎች" ስትወስድ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡
ታይዋንን ከቻይና ወረራ ለመጠበቅ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደንን ጨምሮ የተለያዩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሲዝቱ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ታይዋንን እንደ አንድ ሀገር ለመገንጠል ጫፍ ላይ እንዳለች የግዛት አካሏ አድርጋ የምትመለከተው ቻይና በበኩሏ፤ አስፈላጊ ከሆነ በጉልበትም ልትመልሳት እንደምትችል በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ ትደመጣለች፡፡
የቻይና መንግስት ታይዋን ወደ ሀገሪቱ የምትቀላቀልበትን ዕቅድ ይፋ እስከማድረግ የደረሰበት አጋጣሚም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
እናም ደሴቲቱ ጋር መደበኛ የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንኳን የሌላት አሜሪካ ለታይዋን የምታደርገው ድጋፍ ቀጠናውን ወደለየለት ግጭት እንዳይወስደው ተሰግቷል፡፡