የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር በኪቭ ድንገተኛ ጉብኝት አደረጉ
የፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል
ፍራንክ ዋልተር ለዩክሬናውያን ባስተላለፉት መልዕክት “ከጎናችሁ ነን ጀርመን መተማመን ትችላላችሁ" ብለ
የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር በኪቭ ድንገተኛ ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
ጉዞው በየካቲት ወር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች የመጀመሪያ ጉብኝት መሆኑ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ በላኩት መግለጫ መሰረት ፍራንክ ዋልተር "ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር በኪቭ ለመገናኘት በጉጉት እጠብቃለሁ" ብለዋል።
ሽታይንማየር ከዜለንስኪ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በቤላሩስ ድንበር አቅራቢያ የምትገኝና በቅርቡ ነጻ የወጣቸው ግን ደግሞ ብዙ የኢነርጂ መሰረተ ልማቶች ውድመት ያጋጠማትን ከተማን እንደሚጎበኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሽታይንማየር ለከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ለኢነርጂ መሰረተ ልማት የሚሆን ርዳታ እንደሚሰጡም ይጠበቃል፡፡
"ለዩክሬናውያን ያለኝ መልእክት ቢኖር በጀርመን መተማመን ትችላላችሁ" ሲሉም ተናግረዋል ሽታይንማየር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ በጀመረች ወራት ውስጥ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሽታይንማየር ለዓመታት ከሞስኮ ጋር ባሳዩት መቀራረብ ምክንያት ከፍተኛ ትችት ቀርቦባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዚህም አላበቃም ፕሬዝዳንቱ በሚያዝያ ወር ኪቭን ለመጎብኘት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱ በጀርመንና ዩክሬን መካከል ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ በወቅቱ እንደተናገሩትም፤ የኪቭ ሽታይንሜየርን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ እሳቸው በዩክሬን ለማድረግ አቅደውት የነበረውን (በሰኔ ወር ከጣሊያን ማሪዮ ድራጊ እና ከፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ያደረጉት ጉብኝት) የሚያደናቅፍ ነው ብለው ነበር፡፡
ያም ሆኖ ከሞስኮ ጋር በነበራቸው ግንኙነት ተያያዞ የሚነሳው ትችት ትክክል እንደነበር ያመኑት ፕሬዝዳንት፤በዩክሬን ላይ የተጀመረውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ ከክሬምሊን ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ማቋረጣቸው ይነገራል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የጀርመን ፕሬዚደንት ሆነው ያገለገሉት የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ተወካይ ሽታይንማየር በቀድሞው ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በሁለቱ መንግስታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡
የጀርመን መራሄ መንግስት “ሩሲያ ከዩክሬን ምድር ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ” ፑቲንን ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
ኦላፍ ሾልዝ ከፑቲን ጋር በነበራቸው 90 ደቂቃ በፈጀ የስልክ ቆይታ ፤ “ፑቲን በተቻለ ፍጥነት ተኩስ አቁመው ወደ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲመጡና ወታደራቸው ሙሉ በሙሉ ከዩክሬን ምድር በማውጣት የዩክሬን ግዛት ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ” ማሳሰባቸው ቃል አቀባያቸው ስቴፈን ሃበስተሬት አስታውቋል፡፡
ኦላፍ ሾልዝ ሀገራቸው ለዩክሬን አዲስ የጦር መሳሪያ ልታበረክት መሆኑን እና በቅርቡ እንደሚላክላት መናገራቸውም ይታወሳል።
ኦላፍ ሾልዝ ሃምሌ ላይ በዩክሬን ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሀገራቸው ዩክሬንን ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ገለጸውላቸው እንደነበርም የሚታወስ ነው።