ፕሬዝዳንት ፑቲን የአደጋው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል
የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስቴር የሩሲያ ቅጥረኛ ጦር ዋግነር ቡድን አዛዥ የተሳፈሩበት አውሮፕላን በሚሳይል ስለመመታቱ የሚሳይ መረጃ እስካሁን የለም ብሏል።
በቅርቡ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ተቃቅረው የነበሩት የዋግነሩ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪ ይቭጂኒ ፕሪጎዚን በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ስለ አደጋው ዝርዝር መረጃም ሆነ አሜሪካ የአደጋው መንስኤ ነው ብላ ስለምታምነው ጉዳይ ማብራሪያ አልሰጡም።
ሮይተርስ ሀሙስ ዕለት አሜሪካ ለአውሮፕላኑ መከስከስ የተለያዩ መንስኤዎችን እየመረመረች መሆኑን ዘግቧል።
የዋሽንግተን ባለስልጣናት ጠቅሶ፤ የአደጋው መንስኤ ወደ አየር የተተኮሰ ሚሳይል ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ዎል ስትሪት ጆርናል ለጉዳዩ ቅርብ ናቸው ያላቸውን ጠቅሶ፤ ለአደጋው የቦምብ ፍንዳታ መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ዘግቧል።
የሩሲያ የአየር ባለስልጣን ሞስኮ አቅራቢያ ፕሪጎዚ፣ ምክትላቸውና ሌሎች ስምንት ሰዎች ይጓዙበት የነበረው የግል አውሮፕላን ተከስክሶ የሁሉም ህይወት አልፏል ብሏል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሀሙስ እለት በአደጋው ማዘናቸውን ጠቅሰው፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የአደጋው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።