የ62 ዓመቱ ፕሪጎዢን በፒተርስበርግ ከተማ ተወልደዋል
የሩሲያው ዋግነር አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዢን ማን ናቸው?
የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዢንንን ጨምሮ 10 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሶ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የሩሲያ አቪዬሽን ባለስልጣን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በአደጋው ሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ማለፉን ገልጾ ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
ለመሆኑ ከ50 ሺህ በላይ የግል ቅጥረኛ ወታደሮች እንዳላቸው የተናገሩት የቨግኒ ፕሪጎዢን ማን ናቸው?
በፈረንጆቹ 1961 በፒተርስበርግ ከተማ የተወለዱት የቨግኒ አብዛኛው የወጣትነት ጊዜያቸውን በሩሲያ እስር ቤቶች አሳልፈዋል።
በ1990 ከእስር ቤት ሲፈቱም ምግብ አብሳይ በመሆን ምግብ ቤት በመክፈት ወደ ንግድ ዓለም የተቀላቀሉት የቨግኒ በወቅቱ የፒተርስበርግ ከተማ ከንቲባ ረዳት ከነበሩት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተዋውቀዋል።
ቢዝነሳቸውን ቀስ በቀስ ያሳደጉት የቨግኒ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ቅርርባቸው እያደገ መጥቶ ዋነኛ አጋር እስከመሆን ደርሰዋል።
በፈረንጆቹ 2014 ዋግነር የተሰኘውን ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን በመመስረትም በሩሲያ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን በቅተዋል።
የሩሲያ መንግስታዊ ኮንትራቶችን በመውሰድ በርካታ ስራዎችን የሰሩት እኝህ ወታደራዊ አዛዥ በተለይም ሞስኮ በውጭ ሀገራት የምታካሂዳቸውን ፍላጎቶች ከማሳካት አንጻር ቁልፍ ሰውም ነበሩ።
በተለይም በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በዩክሬን እና በምዕራብ አፍሪካ የሩሲያ የሀይል ሚዛን እንዲኖራት በማድረግ ስኬታማው ሰው እንደሆኑ ተገልጿል።
አሁን ላይ በሩሲያ ውስጥ አምስተኛው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው የሆኑት የቨግኒ ፕሪጎዢን በዩክሬኗ ቁልፍ ስፍራ ባክሙት የተደረገውን ከባድ ጦርነት በድል ተወጥተዋል።
ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ እሳቸው እና ጦራቸው በሩሲያ መከላከያ ላይ በማመጽ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ግጭት ውስጥ ገብተውም ነበር።
በአዛዡ ላይም የሀገር ክህደት ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ በቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሌኮሼንኮ አደራዳሪነት አመጹን ሲያቋርጡ በእሳቸው ላይ የተመሰረተባቸው ክስም እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ከይቅርታው በኋላ ዳግም ዋግነርን መምራት የጀመሩት ፕሪጎዢን ከሰሞኑ ትኩረታቸውን ወደ አፍሪካ እንዳደረጉ ተናግረውም ነበር።