አሜሪካ ፤ ቱርክ የአሜሪካ አጋር በሆኑ የሶሪያ ኩርዶች ላይ እየፈጸመች ያለውን ጥቃት ተቃወመች
የኢስታንቡል የቦምብ ጥቃት ተከትሎ ቱርክ የኩርድ ኃይሎች ተጠያቂ ማድረጓ ይታወቃል
የሶሪያ ኩርዶች ከ2015 ጀምሮ አይኤስን በመዋጋት ላይ የተሰማሩ ኃይሎች መሆናቸው ይነገራል
አሜሪካ ፤ ቱርክ የአሜሪካ አጋር በሆኑ የሶሪያ-ኩርዶች ላይ እየፈጸመች ያለውን ጥቃት ተቃወመች፡፡
ከሳምንት በፊት በኢስታንቡል የቦምብ ጥቃት ስድስት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ቱርክ ለድርጊቱ በሶሪያ የሚገኙትና የአሜሪካ አጋር የሆኑት የኩርድ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡
በዚህም አላበቃም ቱርክ በአሜሪካ አጋር በሆኑት ኩርድ ቁጥጥር ስር ባሉ ቦታዎች ላይ ድንበር ተሻጋሪ የአየር ድብደባዎችን እና የሚሳይሎችን ጥቃት ስትሰነዝር ቆይታለች፡፡
በዚህም የቱርክ አውሮፕላኖች በሰሜናዊ ሶሪያ በሰነዘሩት ወታደራዊ ጥቃት ንጹሃን ሰዎች ጭምር መገደላቸው ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡
ጉዳዩ እጅጉን ያሳሰባት አሜሪካም ታዲያ ኢስታምቡል የአሜሪካ አጋር በሆኑት የሶሪያ ኩርዶች ላይ እየፈጸመች ያለችውን ጥቃት ከዩክሬን ጦርነት ጋር አመሳስለዋለች፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ቱርክ በሰሜናዊ ሶሪያ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ዋሽንግተን አጥብቃ እንደምትቃወም ለቱርክ አቻቸው ገልጸውላቸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የጆ-ባይደን አስተዳደር ሩሲያን ለመቃወም በተለይም ቱርክ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶ እንዳይቀላቀሉ ያላትን ተቃውሞ እንድታቆም ለማሳመን ከሌሎች የኔቶ አጋሮች ጋር የኤርዶጋንን ትብብር እንሚፈልግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ሲል ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
የሶሪያ -ኩርዶች እንደፈረንጆቹ ከ 2015 ጀምሮ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች ጋር በመሆን አይኤስ ን በመዋጋት ላይ የተሰማሩ ኃይሎች መሆናቸው ይነገራል፡፡
ለዚህም ከአሜሪካ ጦር ጋር የተለያዩ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች እንደሚያደርጉም ጭምር ይገለጻል፡፡
ቱርክ ግን የሶሪያ ኩርዶች በደቡብ ምስራቅ ቱርክ ከሚገኘው የኩርድ ፒኬኬ አማጽያን ጋር በመተባበር ለአራት አስርት አመታት የዘለቀውን እና በሁለቱም ወገኖች በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ታጣቂዎች አጋር መሆናቸውን ስታናገር ትደመጣለች።
ኢስታምቡል ለንጹሃን ደም የሶሪያ ኩርዶችን በተለያዩ ጊዜያት ተጠያቂ ስታደርግ ብትደመጥም ኩርዶቹ ግን በቱርክ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃት ይክዳሉ።