ጆ ባይደን፤ በቻይና ላይ የተጣሉ ታሪፎችን ለማንሳት እያሰቡ መሆኑን ገለጹ
አሜሪካ በቤጅንግ ላይ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የቻይና እቃዎች ላይ ታሪፍ ጥላ ነበር
ፕሬዝደንት ባይደን፤ ታሪፎቹን “እኛ አልጨመርንም” ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፤ ከእርሳቸው በፊት የነበረው አስተዳደር በቻይና ላይ ጥሏቸው የነበሩ የንግድ ታሪፎችን ለማንሳት እየታሰበ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በእስያ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጋር በሰጡት መግለጫ ዋሸንግተን፤ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጊዜ በቤጅንግ ላይ የጣለቻቸውን ታሪፎች ለማንሳት እየታሰበ ስለመሆኑም ነው ጥቆማ የሰጡት፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን “እኔ እያሰብኩበት ነው፤ እኛ ምንም ታሪፍ አልጣልንም፤ ታሪፎቹ የተጣሉት በቀደመው አስተዳደር ነው፤ አሁን ግን እያሰብንበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በ 2018፤ የአሜሪካ እና የቤጅንግ የንግድ ጦርነት በተካረረበት ወቅት አሜሪካ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የቻይና እቃዎች ላይ አዲስ ታሪፍ ጥላ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የእጅ ቦርሳዎች፣ ሩዝ፣ ጨርቃጨርቅና ሌሎች በድምሩ ስድስት ሺህ የሚሆኑ እቃዎች ላይ ታሪፍ ጥላ የነበረ ቢሆን ጆ ባይደን ግን እነዚህ እየታሰበባቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በቻይና ላይ ለጣሉት ታሪፍ በምክንያትነት ያቀረቡት ቻይና ኢፍትሃዊ የንግድ አሰራር እያሳየች ነው የሚል መሆኑም ይታወሳል፡፡
ቻይና፤ ኩባንያዎቿን መደጎሟ እና ቻይና ውስጥ በተወሰኑ ዘርፎች የሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች የግድ አንድ የአገር ውስጥ አጋር እንዲኖራቸው ማስገደዷ አሜሪካን አላስደሰታትም ነበር፡፡ ቻይናም በወቅቱ አጸፋውን እመልሳለሁ ስትል መቆየቷ ይታወሳል፡፡