በዝንጀሮ ፈንጣጣ ብዙ ዜጎቿ የተያዙባት ሀገር አሜሪካ መሆኗ ተገለጸ
በሽታው እስካሁን በ 75 ሀገራት መከሰቱ ተነግሯል
በዓለም እስካሁን 18 ሺ ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ ተይዘዋል
በአሜሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በሌላ ሀገር ካሉት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን የሀገሪቱ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል አስታወቀ፡፡
ማዕከሉ እንዳስታወቀው ከሆነ በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙት ሰዎች ቁጥር አንድ ሺ ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥር አሁን ላይ በየትኛውም ዓለም ካለው የበለጠ መሆኑን ማዕከሉ ገልጿል።
የበሽታ በከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በበኩሉ በአሜሪካ በአጠቃላይ 1 ሺ 48 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አስታውቋል፡፡ በአጠቃል በአሜሪካ 4 ሺ 639 ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ መያዛቸው ታውቋል፡፡ እስካሁን በ 75 ሀገራት የሚገኙ ከ 18 ሺ በላይ ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ መያዛቸው ተገልጿል፡፡
አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ መረጃ መሰረት በዝንጀሮ ፈንጣጣ ብዙ ዜጎቿ የተያዙባት ሀገር አሜሪካ ስትሆን ስፔን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በጀርመንና ብሪታኒያም የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን በጠቅላላ በአውሮፓ ደግሞ በሶስት እጥፍ ጨምሮ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ኃላፊ፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ እየጨመረ መትቷል ሲሉ ከሶስት ሳምንታት በፊት ገልጸው ነበር፡፡
ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ባለፈም የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በአፍሪካ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቆ ነበር፡፡ ድርጅቱ ሰኔ መጀመሪያ አካባቢ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት 1 ሺ 400 ሰዎች በአዲሱ የፈንጣጣ በሽታ ዝርያ (ሞንኪ ፖክስ) መያዛቸውን ገልጾ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ለመለየት የሚያስችሉ 50 የላብራቶሪ ማዕከላት ተደራጅተዋል