ፈረንሳይ ከሩሲያ የምታገኘውን ነዳጅ በሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ መተካት እንደምትፈልግ ገለፀች
የፈረንሳዩ ማክሮን የሳዑዲ አረቢያ ልዑል አልጋወራሽ ቢን ሳልማንን በኢሊሴይ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋገሩ
መሪዎቹ ፡ በነዳጅ፣ በኢራን ኒውክሌር ማበልጸግ ጉዳይ እንዲሁም የመብት ጉዳይ ላይ ተወያይቷል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሳዑዲ አረቢያ ልዑል አልጋወራሽ ሞሀመድ ቢን ሳልማንን ተቀብለው አነጋገሩ።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ የነዳጅ፣ የኢራን ኒውክሌር ማበልጸግ ጉዳይ እንዲሁም የመብት ጉዳይ መሪዎቹ ከመከሩባቸው አበይት ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።
የሳዑዲው ልዑል አልጋወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን የፓሪስ ጉብኝት፤ ጆ-ባይደን በሪያድ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ካደረጉና ከሳዑዲ ባለስልጣነት በተለያዩ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መክረው ከተመለሱ በኋላ የተደረገ መሆኑ ነው።
እናም የምዕራባውያኑ ሩጫ፤ አስጊ ወደመሆን የደረሰውን ከኢራን ሊጋረጥ የሚችለው የኒውክሌር ማበልጸግ ጉዳይ፣ የሩሲያ እና ቻይና ቀጣናዊ ተጽእኖ ለመመከት እንዲሁም ከባህረ ሰላጤው የዓረብ ሀገራት የነዳጅ ዘይት ድርጅት /ኦፔክ/ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደገና ለመጀመር እንደሚፈልጉ የሚያመላክት እንደሆነ የጂኦ-ፖለቲክስ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ፣ ሞስኮ ለአውሮፓ የምታቀርበውን የጋዝ በመቆራረጡ ምክንያት የሃይል ምንጫቸውን ለመቀየር እየፈለጉ እንደሆነም ነው የሚነገረው።
በዚህም በዓለም ትልቁ የነዳጅ ዘይት ላኪ የሆነቸው ሪያድ ምርቷን እንድታሳድግ የፈረንሳይ ፍላጎት መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከኢራን ጋር በቀጣናው አቀፍ የሰላም ስምምነት እንዲፈጠር በሚደረገው ጥረት እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ካሉ እስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ፈረነሳይ ሳዑዲ አረቢያን እንደ ዋነኛ አጋዥ ሚና ያላት ሀገር አድርጋ ትመለከታታለች።
ፈረንሳይ ለሪያድ የጦር መሳሪያ ከሚያቀርቡ ዋነኛ ሀገራት አንዷ ብትሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሳዑዲ ላይ ከሚሰተዋሉ የሰብዓዊ ቀውሶች እና በየመን (ከሁቲ አማጽያን ጋር የሚደረግ ውጊያ) እየተከሰተ ባለው የሰብአዊ ቀውስ ሳቢያ ሽያጩን እንድትገመግም ተገዳለች።