አሜሪካ በአየር ንብረት ጉዳይ እንነጋር ስትል ቻይናን ጠየቀች
ጆን ኬሪ ወደ ታዳሽ ኃይል በሚደረገው የሽግግር ሂደት እውን ለማድረግ የግሉን ሴክተር ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል
አሜሪካና ቻይና የዓለማችን ከፍተኛውን የግሪን ሀውስ ጋዝ የሚለቁ ሀገራት ናቸው
የአሜሪካ የአየር ንብረት መልዕክተኛ ጆን ኬሪ፣ ቻይና የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመከላከል የሁለትዮሽ ንግግሮችን እንድትቀጥል ጠየቁ፡፡
ጆን ኬሪ በሃኖይ ከሚገኙ የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች ቡድን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፤የዓለማችን የፈረጠመ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑትና ከፍተኛውን የግሪን ሀውስ ጋዝ የሚለቁት አሜሪካና ቻይና የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶችን ለመቅረፍ በጋራ መስራት አለባቸው ሲሉ መናገራቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
"ተስፋዬ ፕሬዝዳንት ዢ ከእኛ ጋር ወደ ጠረጴዛው እንዲመለሱና ይህን ዓለም አቀፍ ስጋት ለመቋቋም በጋራ እንድንሰራ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል ኬሪ፡፡
የዓለምን ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ የመገደቡን እቅድ እውን እንዲሆን፤ የግሉ ሴክተር ወደታዳሽ ኃይል በሚደረገው የሽግግር ሂደት ላይ የሚያፈሰው ኢንቨስትመንት እንዲያሳድግም ጠይቀዋል ኬሪ፡፡
ጆን ኬሪ፤ "ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገውን ሽግግር ፈንድ ለማድረግ በቂ ገንዘብ ያለው መንግስት በምድር ላይ የለም " ብለዋል፡፡
ይህንን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ “የግሉን ሴክተር ወደ ጠረጴዛው ማምጣት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ በቅርቡታይዋንን መጎብኘታቸው ያስቆታት ቻይና፤ በአየር ንብረት፣ በጸጥታ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር ምታደርገው ትብብር ማቋረጧ አይዘነጋም፡፡