ዲፕሎማቱ በተለይም በሶሪያና ሊባኖስ ቀውሶች ዋና ልዑክ በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል
አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ሹም ጄፍሪ ፊልትማን በአራት ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ዛሬ ይጀምራሉ፡፡
ልዩ መልእክተኛው ጄፍሪ ፊልትማን ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት በሚኖራቸው የአፍሪካ ቀንድ ቆይታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ግብፅ፣ኤርትራ እና ሱዳን እንደሚያቀኑም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት የሚያመክተው፡፡
ጄፍሪ ፊልትማን በቆይታቸው ከሀገራቱ መንግስታት እንዲሁም አፍሪካ ህብረት ኃላፊዎች ጋር ይመክራሉ ተብለዋል፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ተወካዮችም ጋርም ይወያያሉ ተብሏል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ የአሜሪካ አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የተወሳሰበ የፖለቲካ ፣ የፀጥታ እና የሰብአዊ ቀውሶችን ለመፍታት የሚያስችል ዘላቂ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴን ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያጎላ ነውም ብለዋል፡፡ ልዩ መልእክተኛው አሜሪካ በቀጠናው ለማራመድ የምታስበውን ፖሊሲ እንደሚያስተባብሩም ጭምር፡፡
ጄፍሪ ፊልትማን አንጋፋ ዲፕሎማት ሲሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካና የፀጥታ አማካሪ በመሆን ስርተዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለይም በሶሪያና ሊባኖስ ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲመጣ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ዋና ልዑክ በመሆን አገልግለዋል።