አሜሪካ ቻይና ላይ ማዕቀብ ለመጣል የአጋሮችን ድጋፍ እየፈለገች ነው ተባለ
ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ቻይና ለሩስያ የጦር መሳሪያ ለማቅረብ እያሰበች ነው ሲሉ ከሰዋል
አሜሪካ ቻይና ለሩሲያ እርዳታ እንዳታቀርብ በቀጥታ አስጠንቅቃለች
አሜሪካ ቻይና ላይ ማዕቀብ ለመጣል የአጋሮችን ድጋፍ እየፈለገች ነው ተባለ።
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ቤጂንግ ወታደራዊ ድጋፍ ከሰጠች አዲስ ማዕቀብ ለመጣል አሜሪካ የቅርብ አጋሮቿን እያስማማች ነው ተብሏል።
ሮይተርስ ከምንጮቼ ሰማሁ ብሎ እንደዘገበው ንግግሩ በቅድመ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ማንኛውንም አይነት እገዳ ለማድረግ በተለይም ከቡድን ሰባት ሀብታም ሀገራት ድጋፍ ለማግኘት ማስማማትን ያለመ ነው።
ዋሽንግተን ምን የተለየ ማዕቀብ ለመጣል እንዳሰበች ግልጽ አይደለም ተብሏል።
ማዕቀብ የመጣል ኃላፊነት ያለው የአሜሪካ የግምጃ ቤት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ባለፉት ሳምንታት ቻይና ለሩስያ የጦር መሳሪያ ለማቅረብ እያሰበች ነው ሲሉ ቢናገሩም ቤጂንግ ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
የዋሽንግተን ባለስልጣናት ቻይና እርዳታ እንዳታቀርብ በቀጥታ አስጠንቅቀዋል።
በአሜሪካ የማዕቀብ ምክክር የተሳተፉ አንድ ባለስልጣን ቻይናን በተመለከተ ለሩሲያ ወታደራዊ እርዳታ ልትሰጥ እንደምትችል የሚጠቁም ጥቂት መረጃ ብቻ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ግን የስለላ መረጃውን ለአጋሮች በዝርዝር እያቀረብን ነው ብለዋል።
ባይደን አርብ በዋይት ሀውስ ከጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልስ ጋር ሲገናኙ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ውስጥ የቻይና ሚና ከውይይት ከርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት ቻይና በምዕራቡ ዓለም ጥርጣሬ ውስጥ የገባ አጠቃላይ የተኩስ አቁምን የሚጠይቅ ባለ 12 ነጥብ የሰላም ምክረ ሀሳብ ይፋ አድርጋለች።