ቻይና ታይዋንን በሃይል ለመያዝ መዘጋጀቷን የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ገለጸ
የቻይናው ፕሬዝዳንት ወታደሮቻቸው ከአራት አመት በኋላ ታይፒን ለመውረር እንዲዘጋጁ ማዘዛቸውንም ሲ አይ ኤ ደርሼበታለሁ ብሏል
ዋሽንግተን ራስ ገዟን ታይዋን ከቤጂንግ ወረራ ለመታደግ እርምጃ እንደምትወስድ መዛቷ ይታወሳል
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ወታደሮቻቸው በፈረንጆቹ 2027 በታይዋን ላይ ለሚፈጸም እርምጃ ዝግጁ እንዲሆኑ ማዘዛቸውን የአሜሪካ የስለላ መረጃዎች ማመላከታቸው ተገለጸ።
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) ዳይሬክተሩ ዊሊያም በርንስ እንዳስታወቁት፥ ጂንፒንግ ታይፒን ሙሉ በሙሉ በሃይል ለመቆጣጣር ዝግጅት ማድረጋቸውንን ቀጥለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የገጠማት ፈተና ስጋት ሳያጭርባቸው እንዳልቀረ የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፥ ሆነም ቀረም ታይዋንን በሃይል የመያዝ ወረራው አይቀሬ ስለመሆኑ የስለላ መረጃዎቻችን አመላክተዋል ብለዋል።
ከሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት ዊሊያም በርንስ፥ ዋሽንግተን ይህን የቤጂንግ እቅድ በዋዛ ልትመለከተው እንደማይገባ አሳስበዋል።
“ፕሬዝዳንት ሺ ወታደራዊ አዛዦችን ሰብስበው ለ2027ቱ ዘመቻ እንዲዘጋጁ ቢያዙም ከዚያ አስቀድመው እንደማያደርጉት ምንም ማረጋገጫ የለንም፤ ነገር ግን በአጭር ጊዜ መፈጸም እንደማይችሉ ጥርጣሬያቸው ጎላ ያለ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ቻይና እና ታይዋን በ1949ኙ ጦርነት የኮሙዩኒስት ፓርቲ ዋናውን ቻይና፤ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ ታይዋንን ሲይዙ መለያየታቸው ቢጀምርም የቤጂንግ ሹማምንት ታይፒን እንደ ሉአላዊ ሀገር አይመለከቷትም።
የመንግስታቱ ድርጅትም ሆነ ሌላ ሀገርም ለታይዋን ነጻ ሀገርነት እውቅናን አልሰጡም።
የአሜሪካው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተርም በፈረንጆቹ 1979 ለቤጂንግ መንግስት እውቅና ሲሰጥ ከታይዋን ጋር የነበረውን ግንኙነት ማቋረጡ የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ ኮንግረንስ ግን ከታይፒ ጋር ሊኖር የሚችልን ግንኙነት የሚመራ ስምምነትን ማጽደቁን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደርም ቻይና በታይዋን ላይ የሃይል እርምጃ የምትወስድና በወረራ የሉአላዊ ግዛቷ አካል ለማድረግ ከሞከረች ከታይፒ ጎን እንደሚሰለፍ በተደጋጋሚ ገልጿል።
የሲ አይ ኤ ዳይሬክተሩ አሜሪካ ወደ ታይዋን ወታደሮቿን መላክ ስለማሰቧ ግን ያሉት ነገር የለም።
ምዕራባውያን በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለኬቭ ያሳዩት ድጋፍ ቤጂንግን ቆም ብላ እንድታስብ ሳያደርጋት እንዳልቀረ የጠቀሱት ዊሊያም በርንስ፥ ይሁን እንጂ “ለአፍታ አይናችን ከቤጂንግ ላይ ማንሳት የለብንም” ብለዋል።
ራስ ገዟን ወደብ የሉአላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ቻይና ግን ለሲ አይ ኤ ወቀሳ ምላሽ አልሰጠችም።