ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ፣ ቱርክ እና ህንድ ላይ ጥላው የነበረውን የጉዞ እገዳ አነሳች
ሳዑዲ አረቢያ እገዳ ከጣልባቸው ሀገራት ኢትዮጵያ፣ቬትናም፣ህንድ እና አረብ ኢምሬትስ ይጠቀሳሉ
ሳዑዲ አረቢያ እገዳውን ያነሳቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያለበት ሁኔታን ከገመገመች በኋላ ነው ተብሏል
የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ፣ ቱርክ፣ ህንድ እና ቬትናም ላይ ጥለውት የነበረውን የጉዞ እገዳ ማንሳታቸው አስታወቁ፡፡
ሳውዲ አረቢያ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች መብዛታቸውን ተከትሎ፤ ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ 3 ቀን 2021 ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት ሀገራት ተጓዦች ላይ የጉዞ እገዳ ጥላ እንደነበር አይዘነጋም።
ሳዑዲ አረቢያ እገዳ የጣለችባቸው ሀገራት ኢትዮጵያ፣ቬትናም፣ህንድ እና አረብ ኢምሬትስ እንደነበሩም የሚታወስ ነው፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ በተጨማሪም ዜጎቿ ወደ ሶስቱ አገራት እንዳይበሩም የከለከለች ሲሆን እገዳው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚል የወሰነችው እርምጃ እንደነበር በወቅቱ አስታውቃለች፡፡
ይሁን እንጅ አሁን ላይ የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት በሀገራቱ ላይ ጥለውት የነበረውን የጉዞ እገዳ ማንሳታቸው እየተገለጸ ነው፡፡
የሳኡዲ ፕሬስ ኤጀንሲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የሳዑዲ መንግስት የጉዞ እገዳውን ያነሳው ሀገሪቱ ጤና ሊሂቃን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያለበት ሁኔታን በጥልቀት ገምግመው ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ ነው ብሏል፡፡
በዚህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ፣ ቱርክ፣ ቬትናም እና ህንድ የሚያደርጉት ጉዞ የሚያስቀረው እገዳ እንዲነሳ ተወስኗል ይላል ዘገባው።
ሳዑዲ አረቢያ፤ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት በተለያዩ ሀገራት ላይ ጥላው የነበረ እገዳ ስታነሳ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡
ቀደም ሲል በሌሎች 11 ሀገራት ላይ ጥላ የነበረውን የጉዞ እገዳ ማንሳቷን የሚታወስ ነው፡፡
አረብ ኢምሬትስ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን ፖርቹጋል፣ ብሪታኒያ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ እና ጃፓን ላይ ቀደም ሲል በሳዑዲ አረቢያ ተጥሎ የነበረው የጉዞ ክልከላ ከተነሳለቸው ሀገራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡