አሜሪካ በሶሪያ ከ900 በላይ ወታደሮች ያሏት ሲሆን፥ የአል አሳድ ተቃዋሚ ሃይሎችን እንደምትደግፍ ይነገራል
በሶሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ኢራን ሰራሽ ድሮን መቶ መጣሉን አስታውቋል።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ እንዳስታወቀው፥ የስለላ ድሮኗ ኮኖኮ በተባለው ወታደራዊ ጣቢያ ነው ተመታ የወደቀችው።
የወደቀችው ድሮን ባለቤት ነኝ ያለ አካል እስካሁን ባይገኝም በአካባቢው በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት በማድረስ የሚታወቁት በኢራን የሚደገፉ የአይ ኤስ ክንፍ አባላት ንብረት እንደምትሆን ተገምቷል።
በሶሪያ ከ900 በላይ ወታደሮች ያሏት ዋሽንግተን፥ አይ ኤስን የሚዋጉ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎችን እንደምትደግፍ ይታወቃል።
በዚህም በወታደራዊ ጣቢያዎቿ ላይ ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራዎችን ማስተናገዷን የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ አስነብቧል።
በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ከደረሰው ርዕደ መሬት በኋላ ጋብ ብሎ የሰነበተው የእርስ በርስ ጦርነት፥ ወደቀደመው ገጽታው ዳግም ሊመለስ መሆኑን የትናንቱ የድሮን ስለላ አመላካች ነው ተብሏል።
በርካታ ሚኒስትሮቻቸውን ይዘው በቻይና የሶስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ቤጂንግ የገቡት የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናቶች ስለአሜሪካ የድሮን መጣል ዜና የተናገሩት ነገር የለም።
ኢራን በሶሪያ የበሽር አል አሳድ መንግስት እና የተፋላሚ ሃይሎችን ታስታጥቃለች የሚል ወቀሳ ከእስራኤልና ከአሜሪካ በኩል ይቀርብባታል።
ቴህራን የባለፈውን ሳምንት የርዕደ መሬት አደጋ እንደ ሰበብ ተጠቅማ ከአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ይልቅ የጦር መሳሪያዎቿን ወደ ሶሪያ ልታስገባ ትችላለች የሚል ስጋታቸውንም ገልጸዋል።
እስራኤል በበኩሏ12 አመታትን ባስቆጠረው ጦርነት ገለልተኛ አቋም አለኝ ብትልም የቴህራንን የቀጠናው ተጽዕኖ ለመግታት በሚል በሶሪያ ምድር በተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ፈጽማለች።
ሶሪያን የመሻኮቻ ሜዳ ያደረጉት ሁለቱ ባላንጣ ሀገራት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዳግም ወደ ስልጣናቸው ከተመለሱ በኋላ መካሰሳቸው ጨምሯል።
ኢራን ኢስፋን በተባለው ወታደራዊ ፋብሪካዋ ላይ በእስራኤል የድሮን ጥቃት ተቃጥቶብኛል ካለች በኋላም የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት መቆየቷን ወልስትሪት ጆርናል አስታውሷል።
በኢስፋን የተሞከረው የድሮን ጥቃትም ሩሲያ እና ኢራን በዩክሬን ጦርነት የሚውሉ ድሮኖችን በስፋት ለማምረት የጀመሩትን ጥረት ለማሰናከል ያለም ስለመሆኑ ተነግሯል።
በሶሪያ ምድር በሁለት ጎራ በእጅ አዙር ጦር የሚማዘዙት ኢራን እና እስራኤል በዩክሬን ምድርም ይህንኑ እንዲደግሙት የሚያበረታቱ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው።
የእስራኤል መንግስት ግን እስካሁን ከኬቭ ጎን እንዲሰለፍ ለቀረበለት ግብዣ የሰጠው ግልጽ ያለ የይሁንታ ምላሽ የለም።