ደቡብ ኮሪያ የጸረ ድሮን ወታደራዊ ልምምድ አደረገች
20 ተዋጊ ጄቶች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ የአየር መቃወሚያዎች እንዲሁም የጠላት ተደርገው የተሳሉ ድሮኖች በልምምዱ ተሳትፈዋል
አምስት የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች እሰከ ሴኡል ዘልቀው ሳይመቱ ወደ ፒዮንግያንግ ከተመለሱ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው ልምምዱ የተደረገው
ደቡብ ኮሪያ በዛሬው እለት ልዩ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ተገልጿል።
የልምምዱ ዋነኛ ትኩረትም ድሮኖችን ለመጣል የሚወሰዱ እርምጃዎች ናቸው ተብሏል።
20 ተዋጊ ጄቶች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ የአየር መቃወሚያዎች እንዲሁም የጠላት ተደርገው የተሳሉ ድሮኖች በልምምዱ እንዲሳተፉ ተደርጓል መባሉንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያ አምስት ድሮኖች እሰከ ሴኡል ዘልቀው ከአምስት ስአታት ቆይታ በኋላ ያለምንም ጉዳት ወደ ፒዮንግያንግ ከተመለሱ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው ልምምዱ የተደረገው።
ደቡብ ኮሪያ ድሮኖቹ ላይ ከ100 በላይ የማስጠንቀቂያ ተኩሶችን ከፍታ ከሀገሯ ብታባርራቸውም መታ አለመጣሏ ቅሬታን እንደፈጠረ ነው።
የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ይቅርታን ቢጠይቅም፤ መንግስትም ድሮኖች ላይ የሚሰራ ራሱን የቻለ አደረጃጀት በ440 ሚሊየን ዶላር ቢያዋቅርም ሀገሬው ጥርጣሬው አልቀነሰም ነው የተባለው።
በሴኡል አካባቢ የተካሄደው ልምምድ ከ2017 ወዲህ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።
ድሮኖችን ከረጅም ርቀት የመለየት፣ እንቅስቃሴያቸውን የመከታትልና መምታት ልምምዱ ውጤታማ እንደነበር የሀገሪቱ መከላከያ ገልጿል።
ፕሬዝዳንት የን ሱክ የልም የሰሜን ኮሪያ ጸብ አጫሪነት የአየር መከላከያ ስርአታችን ይበልጥ እንድናጠናክር አድርጎናል ማለታቸው ነው የተነገረው።
ሀገራቸው ለትናንት በስቲያው የፒዮንግያንግ ጸብ አጫሪነት አጻፋ ሶስት ድሮኖችን ወደ ሰሜን ኮሪያ ድንበር መላኳ ቢነገርም ከኪም ጆንግ ኡን ጽህፈት ቤት የወጣ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም።
የሰሜን ኮሪያ ግዥው ሰራተኞች ፓርቲ አመታዊ ስብሰባውን እያደረገ ይገኛል።
የቀጣይ አቅጣጫዎቹን በቀጣዩቹ ቀናት አጽድቆ ይፋ እንደሚያደርም እየተጠበቀ ነው።
በ2022 ክብረወሰን የሆነ ከ64 በላይ የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ በፈረንጆቹ አዲስ አመትም ከጎርቤቶቿ እና የምዕራባውያን አጋሮቻቸው ጋር መነታረኳ አይቀሬ ይመስላል።