አሜሪካ ወደ እስራኤል የላከችው "ኃይለኛው" ታአድ የጸረ- ሚሳይል ስርአት ዝግጁ ነው አለች
ቀኑ አይታወቅ እንጂ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመክፈት ዝግጅቷን ጨርሳለች
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የታአድ ስርአትን ከ100 ወታደሮች ጋር መላኩ እስራኤል ራሷን እንድትከላከል ይረዳታል ብለዋል
አሜሪካ ወደ እስራኤል የላከችው "ኃይለኛው" ታአድ የጸረ- ሚሳይል ስርአት ዝግጁ ነው አለች።
የአሜሪካ ጦር ዘመናዊ የተባለውን የጸረ-ሚሳይል መከላከያ ስርአት ወደ እስራኤል ለመላክ ሲጣደፍ እንደነበር እና አሁን ዝግጁ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ተናግረዋል።
ታአድ ወይም የከፍተኛ ቦታ የጸረ-ሚሳይል መከላከያ ስርአት በርካታ እርከኖች ያሉት የአሜሪካ የአየር መከላከያ ስርአት አካል ሲሆን ጠንካራ ለሆነው የእስራኤል የጸረ-ሚሳይል መከላከያ ስርአት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ተብሏል።
"የታአድ ስርአት ዝግጁ ነው" ብለዋል ኦስቲን።
"ስርአቱን በፍጥነት የመጠቀም ችሎታው አለን፤ እንደምንፈልገው እየሄድን ነው።"
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን 180 ባለስቲክ ሚሳይል ባስወነጨፈችባት ኢራን ላይ የበቀል እርምጃ ትወስዳለች ተብላ ለምትጠበቀው እስራኤል የታአድ ስርአትን ከ100 ወታደሮች ጋር መላኩ እስራኤል ራሷን እንድትከላከል ይረዳታል ብለዋል።
አሜሪካ እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነቱን ከማስፋፋት እንድትጠነቀቅ እና በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች እና የኃይል መሰረተልማቶች ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም ጠይቃለች። ባይደን ባለፈው ሳምንት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እስራኤል መቼ እና እንዴት በኢራን ጥቃት እንደምትፈጽም ጥሩ መረዳት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ነገርገን ባይደን የሁለቱን ሀገራት ጥቃት መመላለስ የማስቆም እድሎች እንዳሉም ገልጸዋል።ኦስቲን "እስራኤል የምትፈጽመው ጥቃት በትክክል ይህን ይመስላል ለማለት ከባድ ነው" ብለዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል ናዳ ያዘነበችው የእስራኤልን የሊባኖስ ወረራ እና የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህግ ግድያ ለመበቀል ነበር።
ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ኢራን ከባድ ስህተት ሰርታለች፤ ዋጋ ትከፍላለች" እና የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም" የሚሉ ዛቻዎችን ማሰማታቸው ይታወሳል።
ቀኑ አይታወቅ እንጂ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመክፈት ዝግጅቷን ጨርሳለች።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል ጥቃት የምትሰነዝርባት ከሆነ የአጸፋ ምላሿ የከፋ እንደሚሆን ዝታለች።