የእስራኤልን የማጥቃት እቅድ የሚያሳይ ሚስጥራዊ ሰነድ ከአሜሪካ ደህንነት ሾልኮ መውጣቱ ተዘገበ
ሰነዶቹ "አምስት አይኖች" ለተባሉት ለአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ኒውዝላንድ እና አውስትራሊያ መጋራት የሚችሉ ናቸው
አሜሪካ ሰነዱ እንዴት እንደወጣ ምርመራ እያካሄደች ነው ተብሏል
የእስራኤልን የማጥቃት እቅድ የሚያሳይ ሚስጥራዊ ሰነድ ከአሜሪካ ደህንነት ሾልኮ መውጣቱ ተዘገበ።
እስራኤል በኢራን ላይ የምትፈጽመውን የበቀል ጥቃት እቅድ ያሳያል የተባለ ጥብቅ ሚስጥራዊ ሰነድ ከአሜሪካ ደህንነት ሾልኮ ወጥቷል ተብሏል።
አሜሪካ፣ እስራኤል ልትፈጽመው የምትችለውን የማጥቃት እቅድ የሚዳስሰው ሚስጥራዊ ሰነድ እንዴት እንደወጣ ምርመራ እያካሄደች መሆኑን ኤፒ ሶስት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኤፒ ያናገራቸው አራተኛው የአሜሪካ ባለስልጣን ሰነዱ ትክክለኛ ይመስላል ብለዋል።
ሰነዶቹ የወጡት ከአሜሪካ ጂኦስፓሺያል ኢንተሊጀንስ ኤጀንሲ ሲሆን እስራኤል ኢራን ባለፈው ጥቅምት አንድ ለፈጸመችባት የባለስቲክ ሚሳይል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት መሳሪያዎቿን ጥቃት ለመፈጸም ወደሚያስቸል ቦታ ማንቀሳቀሷን ጠቅሷል።
ሰነዶቹ "አምስት አይኖች" ለተባሉት ለአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ኒውዝላንድ እና አውስትራሊያ መጋራት የሚችሉ ናቸው።
ጥብቅ ሚስጥራዊ መረጃ የሚል የተጻፈባቸው ሰነዶች በቴሌግራም የተጋሩ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገበው በአሜሪካው የሲኤንኤን ቴሌቪዥን ነው።
ሰነዶቹ ሆነ ተብሎ በአሜሪካ የስለላ ሰራተኞች ወይም በጠለፋ ስለመውጣታቸው እና ሌሎች የሾለኩ ሚስጥሮች ስለመኖራቸው ምርመራ እየተካሄ መሆኑን ኤፒ ያናገራቸው እና ስማቸውን ያልገለጻቸው ባለስልጣን ተናግረዋል።
እኝህ ባለስልጣን ፖስት ከማድረግ በፊት ሰነዶቹን ማግኘት የሚችለው ማነው የሚለውን ለመወሰን ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ሰነዶቹ የወጡት አሜሪካ፣ እስራኤል የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋርን መወገድ ጫና ለመፍጠር እንድትጠቀምበት እና በሰሜን ሊባኖስ ያለውን ጦርነት እንዳታስፋፋ እና ቀጣናዊ ጦርነት እንዳይቀሳቀስ ጥንቃቄ እንድታደርግ እያሳሰበች ባለችበት ወቅት ነው።
ነገርግን የእስራኤል አመራር የኢራን የሚሳይል ጥቃት ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን ባወጣው መግለጫ ሰለሰነዶቹ መረጃው እንዳለው ገልጿል።
ኢራን የሊባኖስ ወረራ እና የሄዝቦላህ መሪ ግድያ ሀሰን ነስረላህን ግድያ ለመበቀል በእስራኤል ላይ የሚሳይል ናዳ ማዝነቧ ይታወሳል።