ቻይና በታይዋን አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ በንቃት እየተከታተልኩ ነው - አሜሪካ
ቤጂንግ በደሴቷ ዙሪያ እያካሄድች ያለ ልምምድ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል
የታይዋን ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ቻይና ከበድ ያለ አጻፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ መዛቷ ይታወሳል
ቻይና በታይዋን አካባቢ የምታደርገው ወታደራዊ ልምምድ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን የሀገሪቱ ጥምር ሃይል በታይዋን ደሴት ሊወሰድ ስለሚችል እርምጃ ልምምዱን ስለመቀጠሉ ዘግቧል።
ከታይዋን ደሴት በ50 ኪሎሜትር ላይ ወደሚገኘው ፉጃን ግዛት ተኩስ መክፈቷም ነው የተነገረው።
ታይዋንን ከፊሊፒንስ በሚለየው ባሺ በተባለው አካባቢም የቻይና የጦር አውሮፕላኖች ልምምዳቸውን ማድረጋቸውን የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዛሬው እለትም ከ58 በላይ የቻይና ተዋጊ ጄቶች እና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እንዲሁም 9 መርከቦች በታይዋን አካባቢ ልምምድ ሲያደርጉ መታየታቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያሳያል።
- የታይዋን ፕሬዝደንት ማስጠንቀቂያውን ወደ ጎን በመተው ከአሜሪካ አፈጉባኤ ጋር ተገናኙ
- ቻይና ፤ አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ቀይ መስመር እንዳታልፍ ስትል አስጠነቀቀች
ታይፒ ከቤጂንግ ሊቃጣ የሚችል የሚሳኤል ጥቃትንም በትኩረት እየተከታተለች መሆኑን ነው ያስታወቀችው።
አሜሪካም ሁኔታውን በንቃት እየተመለከተች መሆኑንና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በቂ ሃይል እንዳላት በመግለጽ ለቻይና ማሳሰቢያ ልካለች።
ከፈረንጆቹ 1979 ጀምሮ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው ዋሽንግተን ደሴቷን ከጥቃት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ታይዋን የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትለው ቻይና ግን ይህን የአሜሪካ “ያልተገባ” ጣልቃገብነት ስትቃወም ቆይታለች።
በቅርቡም የታይዋን ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ያደረጉት ቆይታን በጽኑ ተቃውማ የሶስት ቀናት ወታደራዊ ልምምዱን መጀመሯን ማሳወቋ ይታወሳል።
ባለፉት ሶስት አመታት በየእለቱ የጦር አውሮፕላኖቿን ወደ ታይፒ ለስለላ የምትልከው ቤጂንግ የሳይ ኢንግ ዌን አስተዳደር የመገንጠል ፖለቲካን ያራምዳል ብሎ ያምናል።
ከአሜሪካ መንግስት ጋር የሚደረጉ የቻይናን ሉአላዊነት የሚጋፉ ግንኙነቶችና የጦር መሳሪያ ግዥ ስምምነቶች ወደ ጦርነት ያስገባናል በማለት ስታሳስብ መቆየቷ አይዘነጋም።
ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን የያዘው ወታደራዊ ልምምድ የተካረረውን የታይፒና ቤጂንግ ግንኙነት ወደለየለት ጦርነት ይወስደው ይሆን የሚለውን ስጋት አንሮታል።