ቻይና ፤ አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ቀይ መስመር እንዳታልፍ ስትል አስጠነቀቀች
ታይዋን ፤ ቤጂንግ በታይፔ ላይ የምታደርገው ተደጋጋሚ ትንኮሳ ታቁም ስትል አሳስባለች
የታይዋኗ ፕሬዝዳንት ጻይ ኢንግ-ዌን በቅርቡ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት ጉዞ ውጥረቱን እንዳያብበሰው ተስግቷል
ቻይና ፤ አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ቀይ መስመር እንዳታልፍ ስትል አስጠነቀቀች፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ ለአሜሪካ ባለስልጣናት ታይዋን የቻይና የውስጥ ጉዳይ አይደለችም ማለታቸው “ትርጉም የለሽ” ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ "የታይዋን ጥያቄ የቻይና አንኳር ፍላጎቶች አስኳል፣ የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት የፖለቲካ መሰረት እንዲሁም በቻይና-አሜሪካ ግንኙነት መጣስ የሌለበት የመጀመሪያው ቀይ መስመር ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ቻይና ለ"ሰላማዊ ዳግም ውህደት" መስራቷን ትቀጥላለች፤ነገር ግን ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎችን የመውሰድ መብቷ የተጠበቀ ነው ሲሉም አክለዋል ጋንግ፡፡
"ማንም ሰው የቻይና መንግስት እና ህዝብ ብሄራዊ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ የወሰዱትን ጽኑ ውሳኔ እና ታላቅ ቁርጠኝነት አቅልሎ ሊመለከተው አይገባም" በማለተም ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ቻይና ይህን ትብል እንጅ ታይዋን የቤጂንግን የግዛት ይገባኛል ጥያቄ አንደማትቀበልና የህዝቦቿ የወደፊት እጣፈንታ በራሷ መንገድ እንደምትወስን ስትገልጽ ትደመጣለች፡፡
የታይዋን የመከላከያ ሚኒስትር ቤጂንግ በታይፔ ላይ የምታደርገው ተደጋጋሚ ትንኮሳ እንድታቆም አስጠንቅቀዋል፡፡
የቻይና እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ በምትመራው ታይዋን ውጥረት ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡
በተለይም የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የነበሩት ናንሲ ፔሎሲ የታይፔን ጉብኝት ውጥረቱን ይብልጥ እንዳባበሰው የሚታወስ ነው፡፡
ይህ ብእንዲህ እንዳለ የታይዋኗ ፕሬዝዳንት ጻይ ኢንግ-ዌን በቅርቡ ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ መባሉ የቀጠናው ውጥረት ይበልጥ ወደ ቀውስ እንዳይከተው ተሰግቷል፡፡
ፕሬዝዳንቷ በዋሽንግተን ቆይታቸው የወቅቱን የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኬቨን ማካርቲን ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ሮይተርስ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው፡፡
ይሁን እንጅ የታይዋን መከላከያ ሚኒስትር ቺዩ ኩኦ ቼንግ በ ፕሬዝዳንት ጻይ እና ማካርቲy መካከል ሊደረግ ታቅዷል ስለተባለው ስብሰባ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
ከአሜሪካ ጋር በተገናኘ የሚነዛው ወሬ ቻይና ወታደሮቿን ለመላክ የምትጠቀመው ሽፋን ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ይህ እንደማይሆን (ቤጂንግ ወታደሮቿን እንደማትልክ) ተስፋ እናደርጋለን ያሉት ሚኒስትሩ፤ የታይዋን ጦር በሀገሪቱ ላይ ሊቃጣ ሚችለውን አደጋ ለመቀልበስ ዝግጁ መሆኑም አክለዋል፡፡