“ካልታሰበ ሞት ያዳነኝ የፈጣሪ ጥበቃ ብቻ ነው” - ትራምፕ
ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ከግድያ ሙከራው በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት አሜሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል
ሩሲያ በበኩሏ ከትራምፕ የግድያ ሙከራ ጀርባ የባይደን አስተዳደር አለበት ብላ እንደማታምን ገልጻለች
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ በፈጣሪ ጥበቃ መትረፋቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ የግድያ ሙከራው ከተፈጸመባቸው በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የማይታሰበውን (ሞት) ያስቀረው ፈጣሪ ብቻ ነው” ያሉት ትራምፕ፥ አሜሪካውያን “የጽናትና ጥንካሬ ትክክለኛ ባህሪያቸውን” ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገሪቱ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን እንዲያስጠብቁ በመጠየቅም “ክፉዎች እንዲያሸንፉ ልንፈቅድላቸው አይገባም” ብለዋል።
በፔንሲልቪኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በ20 አመት ወጣት የተተኮሰባቸው ትራምፕ፥ ከወደቁበት ሲነሱ በወኔ ተሞልተው “ታገሉ ታገሉ ታገሉ” ሲሉ መደመጣቸው የጥንካሬያቸው ተመሳሌት ተደርጎ እየተነሳላቸው ነው።
የ78 አመቱ ትራምፕ የ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን እጩ መሆናቸውን ፓርቲያቸው በይፋ ከማሳወቁ ከሁለት ቀን በፊት ነው የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው።
ለህይወታቸው የሚያሰጋ ጉዳት ያልደረሰባቸው ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ብሄራዊ ጉባኤውን በሚያደርግባት ዊስኮንሲን በመሆን መልዕክቶች እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል።
በግድያ ሙከራው ዙሪያ የተለያዩ ሀገራት መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የዋሉ ሲሆን፥ ሩሲያ በህዳሩ ምርጫ ባይደንን የሚፎካከሩት ትራምፕ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ዙሪያ አቋሟን ገልጻለች።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሞስኮ የባይደን አስተዳደር ትራምፕን ከምርጫ ፉክክሩ ውጭ ለማድረግ የግድያ ሙከራውን አድርጓል ብላ እንደማታምን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ “በፍርድ ቤቶች ጭምር እጩ ሆነው እንዳይቀርቡና ፖለቲካዊ ተቀባይነታቸው እንዲቀንስ የተሰሩ በርካታ ስራዎች የትራምፕን ህይወት አደጋ ላይ እንደጣሉት ከውጭ ሆኖ ለሚታዘብ ሁሉ ግልጽ ነበር” ብለዋል ፔስኮቭ።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት ከዴሞክራቶች ተጽዕኖ ስለበዛባት ትራምፕ እንዲመረጡ ትፈልጋለች የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ቢቆዩም ፕሬዝዳንት ፑቲን “ከትራምፕ ይልቅ ይበልጥ ተገማቹ ባይደን እመርጣለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከዘለቁ "የዩክሬንን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ" ማለታቸው አይዘነጋም።