የአሜሪካ የጦር በጀት 858 ቢሊየን ዶላር እንዲሆኑ ሴኔቱ አጸደቀ
የዩክሬኑ ጦርነት የ2023ቱን በጀት ከባለፈው አመት በ10 በመቶ ብልጫ እንዲኖረው ማድረጉ ተጠቅሷል
ታይዋንም ከቻይና ሊቃጣባት የሚችል “ወረራን” ለማስቆም የሚደረግላት ወታደራዊ ድጋፍ የፔንታጎንን በጀት 858 ቢሊየን ዶላር አድርሶታል
የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) የ858 ቢሊየን ዶላር የመከላከያ በጀት አጽድቋል።
በጀቱ ከባለፈው አመት የ10 በመቶ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካቀረበት የ45 ቢሊየን ዶላር ብልጫ ያለው ነው።
የ2023 የመከላከያ በጀት በ83 ሴናተሮች ድጋፍና በ11 ተቃውሞ ጸድቋል።
የተቀሩት ሊብራሎችም የአሜሪካን በየአመቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የሚሄደው የጦር በጀት አደገኛ ነው በሚል ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በጀቱ በሃዋይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ለማምረትና ተጫማሪ ኤፍ35 ተዋጊ ጄቶችን እና የጦር መርከቦችን ለመግዛትም ይውላል መባሉን ሬውተርስ አስነብቧል።
ለወታደሮች የሚደረግ የ4 ነጥብ 6 በመቶ የክፍያ ጭማሪም በጀቱ ከፍ እንዲል ምክንያት ተደርገው ከተጠቀሱት መካከል ይገኝበታል።
አሜሪካ እንደ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት እየተመለከተቻቸው ያሉትን ሩስያና ቻይናን ተጸዕኖ መግታትን ታሳቢ ያደረጉ እርምጃዎችን ለመውሰድም በጀት መድባለች።
ፔንታጎን ዩክሬንን ለመደገፍ በጥቂቱ 800 ሚሊየን ዶላር በጀት እንደሚይዝ ነው የተነገረው።
ድጋፉ እንደሁኔታዎች እየታየ ሊሻሻል እንደሚችል ተገልጿል።
ታይዋንንም በቻይና ሊፈጸምባት ከሚችል “ወረራ” ለመጠበቅ የጦር መሳሪያ እና የደህንነት ማረጋገጫ ድጋፎች እንደሚደረግላት ነው የተጠቆመው።
በጀቱ አሜሪካ ተገዳዳሪዎቿን ለመምታት ከመዘጋጀቷ ባሻገር የውስጥ አቅሟን ለማጠናከርም ሰፊ ትኩርት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
የጦር በጀቱ 1 ትሪሊየን ዶላርን መጠጋቱ አለምን ለተጨማሪ የጦር ፉክክርና ውጥረት ይከታል የሚሉ ወገኖች ግን ስጋታቸውን እያጋሩ ነው።
ሴኔቱ ያጸደቀውን የ858 ቢሊየን ዶላር የመከላከያ በጀት ፕሬዝዳንት ባይደን ፊርማቸቸውን አኑረውበት ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።