አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የጋር የባልስቲክ ሚሳኤል ልምምድ ማድረጋቸውን ገለጹ
ሀገራቱ ልምምድ ከማድረግም ባለፈ “ታክቲካል” ብለው የጠሩትን መረጃ ተለዋውጠዋል
ልምምዱ ከ 2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው
የአሜሪካ፤ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አባላት የባልስቲክ ሚሳኤል መከላከል ልምምድ ማካሄዳቸውን ዋሸንግተን አስታወቀች፡፡
ሶስቱ ሀገራት ወታደራዊ ልምምዱን ያካሄዱት በሃዋይ የባህር ዳርቻ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ይፋ አድርጓል፡፡ የሀገራቱ ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያንና ቻይናን ኢላማ ያደረገ ልምምድ መሆኑን ፖለቲካ ታዛቢዎች እየገለጹ ናቸው፡፡
ዋሸንግተን፣ ቶኪዮ እና ሲዑል ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ሶስቱም ሀገራት ልምምድ ካደረጉ በኋላ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ግንኙነታቸው ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ ሁለቱ የእስያ ሀገራት ግንኙነታቸው የተቀዛቀዘው በታሪካዊ ግጭታቸው ምክንያት ነውም ተብሏል፡፡
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል ስልጣን ከያዙ በኋላ ከጃፓን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ ባለፈም ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያላትን አጋርነት እንደምታጠናክር ገልጸው ነበር፡፡ ወታደራዊ ልምምዱም የተካሄደው በዚሁ የአጋርነት መንፈስ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሶስቱ ሀገራት ወታደራዊ ልምምዱን ያደረጉት በፈረንጆቹ ከነሐሴ ስምንት እስከ 14 መሆኑን ፔንታጎን አስታውቋል፡፡ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን፤ የባልስቲክ ሚሳኤል መከላከል ልምምድ ያደረጉት ሰሜን ኮሪያን ለማስደንገጥ አልመው እንደሆነም እየተገለጸ ነው፡፡
ፔንታጎን፤ ወታደራዊ ልምምዱ የተደረገው የጋራ ጸጥታን ለማስከበርና ዓለም አቀፍ ስርዓትን ለማስከበር መሆኑን ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል፡፡ ልምምድ ያደረጉት ሶስቱም ሀገራት በሶስትዮሽ መረጃ ልውውት ስምምነታቸው መሰረት ታክቲካል ብለው የጠሩት መረጃ መለዋወጣቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ልታጠናክር እንደምትችል ትናንት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡