የሩሲያ የኒውክሌር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ
አሜሪካ ለዩክሬን ረጅም ርቀት ሚሳዔሎችን እሰጣለሁ ማለቷን ተከትሎ ነው የኒኩሌር ልምምዱ ተጀመረው
ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮችና 100 በላይ ጦር መሳሪያዎች በልምምዱ ላይ እየተሳተፉ ነው
የሩስያ የኒውክሌር ኃይል ከሚሳኤል ኃይሎቻቸው ጋር በጋራ በመሆን “የተጠናከረ ወታደራዊ ልምድ እያደረጉ መሆኑ ተገለፀ።
የኒውክሌር ሃይሎች ወታደራዊ ልምምድ በኢቫኖቫ ክልል እየተካሄደ መሆኑን ኢንትራፋክስ የዜና ተቋም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።
የሩሲያ የኒውክሌር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ ዜና የተሰማው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን ዘመናዊ እና ሩሲያ ሊደርሱ የሚችሉ ሮኬቶችን እንደሚልኩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።
የኒውክሌር ኃይል ወታደራዊ ልምምዱ ላይ 1 ሺህ የሩሲያ ጦር አባላት እና 100 የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች እየተካፈሉ መሆኑንም የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የሩስያ ስትራቴጂክ ሚሳኤል ሃይል "የሚሳኤል ስርዓቶችን ወደ ልምምድ ቦታ በማምጣት እስከ 100 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ሰልፎችን ማድረግ የውጊያ ወቅት ልምምዶችን ማካሄዳቸው ተነግሯል።
በልምምዱ ላይ “ያርስ” የሚል መጠሪያ ያለው እና እስከ 6 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚወነጨፍ እና በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ኢላማ መምታት ይችላል የተባለው አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል ተሳትፏል።
የሩሲያ የኒውክሌር ኃይል በዩክሬን እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ከተጀመረ ከሶስተኛው ቀን ጀምሮ በከፍተኛ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንደሆነ ይታወቃል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ሶስት ወራት አልፎታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት የዩክሬን ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን ጨምሮ የንግድ ማሳለጫ ወደቦች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መውደማቸውም ይታወቃል።