አሜሪካ፥ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት 2 ቋሚ መቀመጫዎች እንድታገኝ ድጋፍ አደርጋለሁ አለች
የ1.3 ቢሊየን ህዝብ ባለቤት የሆነችውን አህጉር ቋሚ መቀመጫ መስጠት ከተመድ ማሻሻያ ጋር የሚያያዝ ነው ተብሏል
ህንድ፣ ጃፓን እና ጀርመን በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው እየጠየቁ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳሉ
አሜሪካ፥ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በምክር ቤቱ አፍሪካ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች እና ትናንሽ የደሴት ሀገራት አንድ ተለዋዋጭ ወንበር እንዲያገኙ ግፊት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ጀርመን፣ ህንድ እና ጃፓን በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው እየጠየቁ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡
አምባሳደሯ አፍሪካ ቋሚ ውክልና እንዲኖራት አሜሪካ እንደምትደግፍ ቢናገሩም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አሁን ላይ ከሚገኙት አምስት አባል ሀገራት ውጪ እንዲሰጥ ዋሽንግተን ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል፡፡
በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ከፍተኛ ስልጣን ባለው የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው መጠየቅ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ለበርካታ ጊዜያት በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ድርድር ቢደረገም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ሆኖም በቅርብ ጊዜ ተመድ እያደረገ በሚገኘው ሪፎርም ውስጥ ይህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንደሚገባው የድርጅቱን ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝና አባል ሀገራት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
አለም እና የሀይል አሰላለፏ ምክር ቤቱ ከተመሰረተበት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በብዙ መንገድ ተቀይሯል የሚሉት የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ጉተሬዝ ምክር ቤቱ ይህን ለውጥ አካቶ መጓዝ እንደሚኖርበት እየሞገቱ ይገኛሉ፡፡
በጽጥታው ምክር ቤት የሚደረጉ ማንኛቸውም ለውጦች በመመስረቻ ቻርተሩ መሰረት የአባል ሀገራቱን ሁለት ሶስተኛ ድጋፍ እና የአምስቱን የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ይሁንታ ማግኝት ይኖርበታል፡፡
በ1945 በተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ 11 የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ሲኖሩ በ1965 ወደ 15 ሀገራት አድጎ 5 ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ያላቸው ቋሚ አባላትን እና 10 በየሁለት አመቱ የሚለዋወጡ ሀገራትን በአባልነት ይዞ ዘልቋል፡፡
የጸጥታው ምክርብ ቤት በአለም አቀፋዊ ሰለም እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ትላልቅ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይታወቃል፡፡
የጦር መሳርያ እና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲሁም የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በሀገራት እንዲሰማሩ መፍቀድ ከሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡