አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቦታ ሊኖራት ይገባል - ሙሳ ፋኪ መሃመት
ሙሳ ፋኪ፤ አፍሪካ ለጋራ ጥቅም ከቻይናም ሆነ የተቀረው ዓለም ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል
የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር “በሌሎች ጉዳይ ላይ የተወሰኑ አካላት የሚወሱንበት አካሄድ ፍትሃዊ አይደለም” ብለዋል
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቦታ ሊኖራት ይገባል ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሳ ፋኪ መሃመት ተናገሩ፡፡
ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በአፍሪካ ህብረት ባደረጉት ንግግር ሲሆን ፤ ዓለም አሁንም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በወረሰው የተሳሳተ መንገድ እየሄደ ነው ብለዋል፡፡
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ፍትሃዊ አይደለም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ የአፍሪካውያን ጥቅም የሚረጋገጠው አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ በቂ ቦታ ስታገኝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
17 በመቶ የሚሆነው የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ የአፍሪካ ጉዳይ በተመለከተ መሆኑን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ “1ነጥብ 3 ቢልዮን ህዝብ ያላት አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቦታ ሊኖራት ይገባል” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ መሃማት ዓለም አፍሪካን ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ያገለለ አካሄድ እየተከተለ መሆኑ የገለጹት ሙሳ ፋኪ “በሌሎች ጉዳይ ላይ የተወሰኑ አካላት የሚወሱንበት አካሄድ ፍትሃዊ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሁን ያለው አካሄድ “ተቀባይነት የለውም!” በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ስረዓት ያስፈልገናል ሲሉም አክለዋል ሊቀ መንበሩ፡፡
ሙሳ ፋኪ አፍሪካ ከቻይናም ሆነ ከተቀረው ዓለም ጋር የሚኖራት ግንኙነት የአፍሪካ መርሆችና ጥቅሞች ባከበረ መልኩ እንሚሆንም ለቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸውላቸዋል፡፡
“የአፍሪካን ጥቅሞች ባከበረና የጋራ ጥቅም ላይ በተመረኮዘ አኳሃን ከቻይናም ሆነ ከሌላው ዓለም በትብብር መስራት እንፈልጋለን”ም ብለዋል ሙሳ ፋኪ፡፡
በተያያዘ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙሉ በሙሉ በቻይና ድጋፍ በአዲስ አበባ የተገነባውን የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) መርቀዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት ኪን ጋንግ አዲስ አበበ ሲመጡ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸው መሆኑ ነው፡፡
ቻይና በአፍሪካ የቢሊዮን ዶላሮች ኢንቨስትመንት ፈሰስ የምታደርግ የአፍሪካ አጋር መሆኗ ይታወቃል፡፡