ኢርዶጋን ምክርቤቱ እንዲሻሻል ጥሪ ያቀረቡት አሜሪካ የጋዛን የተኩስ አቁም ውሳኔ ሀሳብ እንዳይጸድቅ ማድረጓን ተከትሎ ነው
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኢርዶጋን የተመድ የጸጥታው መሻሻል አለበት ብለዋል።
ኢርዶጋን የጸጥታው ምክርቤት እንዲሻሻል ጥሪ ያቀረቡት አሜሪካ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር ወይም ቬቶ የማድረግ መብቷን ተጠቅማ እንዳይጸድቅ ማድረጓን ተከትሎ ነው።
- የጸጥታው ምክርቤት የተኩስ አቁም ውሳኔ ሀሳብ አሜሪካ በመቃወሟ ሳይጸድቅ ቀረ
- እስራኤል ከጦርነቱ በኋላ በጋዛ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ቀጣና እንደምትፈልግ ተናገረች
"የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ፍላጎት በአሜሪካ ቬቶ ተደርጓል።ይሄ ፍትህ ነው?"ሲሉ ኢርዶጋን በኢስታንቡል በተካሄደ የሰብአዊ መብት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ኢርዶጋን አክለውም የጸጥታው ምክርቤት መሻሻል እንዳለበት ተናግረዋል።
15 አባላት ካሉት ጸጥታው ምክርቤት ውስጥ 13 በአረብ ኢምሬትስ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የደገፉት ሲሆን ብሪታኒያ ድምጽ ከመስጠት ታቅባለች።
ይህ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበው የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሁለት ወር ያስቆጠረው ጦርነት አለምአቀፍ ቀውስ ደቅኗል ሲሉ የጸጥታው ምክርቤትን ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
"የማያቋርጠው የጋዛ ድብደባ እንዲቆም ካልተባበርን፣ ለፍልስጤማውያን የምናስተላልፈው መልእክት ምንድነው?" ሲሉ በተመድ የአረብ ኢምሬትስ ምክትል አምባሳደር መሀመድ አቡሻሀብ ምክርቤቱን ጠይቀዋል።
"በርግጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ በሌላ የአለም ክፍል ላሉ ንጹሃን የምናስተላልፈው መልእክትስ ምን ነው?" ሲሉ ጥያቄ አስከትለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ተኩስ አቁሙን የሚቃወሙት የሚጠቅመው ሀማሰን ብቻ ነው በሚል ምክንያት ነው።
አሜሪካ ጦርነቱ ጋብ ብሎ ንጹሃን ከጥቃት የሚጠበቁበት መንገድ እንዲመቻች እና ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ባደረሰው ጥቃት ያገታቸው እስራኤላውያን እንዲለቀቁ ትፈልጋለች።
በኳታር አደራዳሪነት ጦርነቱን ጋብ የማድረግ ስምምነት መጣሱን ተከትሎ እየተደረገ ያለው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል።
የእስራኤል እግረኛ ጦር በደቡባዊ ጋዛ መሰጠነሰፊ ጥቃት እያደረሰች ነው።
ሀማስ እስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅ ያደረገችው ሙከራ መክሸፉን እና በክስተቱ ታጋች መሞቱን ገልጿል።