የጸጥታው ምክርቤትን ማሻሻያው ጊዜ አሁን ነው - ጉቴሬዝ
የበለጸጉት ሀገራት በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን የሚያካትት የኢኮኖሚ ስርአት ሊፈጥሩ እንደሚገባም የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ተናግረዋል
የጸጥታው ምክርቤት ሪፎርም እንዲያደርግ የተለያዩ ሀገራት መሪዎቹ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በአምስት ሀገራት በተለይም በአሜሪካ የሚዘወር መሆኑ ይነገራል።
የሃያላኑ ሀገራት ፈላጭ ቆራጭነትን አጠናክሮ ያስቀጠለ ነው የሚባለው የጸጥታው ምክርቤት በተለይ እንደ አፍሪካ ያሉ ግዙፍ አህጉራትን እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ችላ ያለ ነው በሚል ይወቀሳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትና የአፍሪካ ህብረትም የጸጥታው ምክርቤት ሪፎርም እንዲያደርግ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል።
የቡድን 7 አባል ሀገራት ስብሰባ በጃፓን ሄሮሺማ ሲደረግ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር የጸጥታው ምክርቤት የሚሻሻልበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
ምክርቤቱ አሁን ያለውን የአለም እውነታ ያልተረዳ ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፥ በፍጥነት ሪፎርም ሊያደርግ እንደሚገባው አሳስበዋል።
በሄሮሺማ የተካሄደው የቡድን 7 አባል ሀገራት ስብሰባ የ1945ና ያለፈባቸው አለምአቀፍ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ምን ያህል የዘነጉ መሆናቸውን ያሳየ ስለመሆኑም ነው ያነሱት።
በተለይም በአለም ምጣኔ ሃብት ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን ሀገራት የሚያካትት ስብስብ መፈጠር እንዳለበትም በመጥቀስ።
የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዋና ኢኮኖሚስት ፔየር ኦሊቨር በበኩላቸው፥ ቻይና እና ህንድ ከአለም ምጣኔ ሃብት የ2023 እድገት 50 በመቶውን እንደሚሸፍኑ ይገልጻሉ።
የቡድን 7 አባል ሀገራት ያለፉት የ30 አመታት እድገት ግን እየቀነሰ ይገኛል፤ በ1980 ከነበራቸው የአለም እድገት ድርሻ (50 ነጥብ 7 በመቶ) በ2023 ወደ 30 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የበለጸጉት ሀገራት እንድ ህንድ እና ቻይና ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ያካተተ ትብብር ካላደረጉ የእድገት ጉዟቸው ከዚህም የከፋ እንዳይሆን አይኤምኤፍ ገልጿል።
UN chief Security Council reform