አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ 'ለተቸገሩ ሰዎች እየደረሰ አይደለም' በሚል አቆመች
የምግብ እርዳታው በተስፋፋና በተቀናጀ መልኩ ወጀ ሌላ አቅጣጫ እየተወሰደ ነው ተብሏል
እርዳታውን ከተጎጅዎች ማን እየነጠቀ ነው የሚለው አልገለጸም
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ማቋረጡን አስታውቋል።
ድርጅቱ እርዳታው ከተቸገሩ ሰዎች እየተወሰደ ነው ብሏል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ዩኤስኤአይዲ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር "በተስፋፋና በተቀናጀ ዘመቻ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚደርሰው የምግብ እርዳታ ወደ ሌላ አቅጣጫ በመቀየር ላይ ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።
መግለጫው ከዘመቻው ጀርባ ማን እንዳለ ወይም እርዳታው ለማን እንደሚዘዋወር ግን አልገለጸም።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ከ20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከፍተኛውን የሰብዓዊ እርዳታ የምታቀርብ ሀገር መሆኗን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮይተርስ ከአሜሪካ ለለጋሾች ተሰራጭቶ በእጄ አግኘሁት ባለው ሰነድ ድርጅቱ እርዳታው ለኢትዮጵያ "ወታደራዊ ክፍሎች" ተወስዷል ብሎ ያምናል።
"እቅዱ የተቀነባበረው በፌዴራል እና በክልል የመንግስት አካላት ሲሆን በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ወታደራዊ ክፍሎች ከሰብአዊ እርዳታው ተጠቃሚ ይሆናሉ" ሲል ዩኤስኤአይድን ያካተተው የሰብዓዊ እርዳታ እና የመቋቋም ለጋሽ ቡድን ገልጿል።
ሮይተርስ የኢትዮጵያ መንግስት አስተያየት እንዲሰጥ ላቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠኝም ብሏል።
ዩኤስኤአይዲ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ለተጎጅዎች እየደረሰ አይደለም በሚል ባለፈው ወር የምግብ እርዳታቸውን ማቋረጣቸው ይታወሳል።