“ሰብዓዊነት አሳስቦኝ እንጂ፤ እንደሚወራው መንግስት ለመቀየር አልመጣሁም”- ሳማንታ ፓወር፣ የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪ
ከኃላፊነታቸው ጋር የተቀራረበ ስራን ከሚሰሩ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር እንዲወያዩ መደረጉም ነው የተገለጸው
ሳማንታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ምክትላቸውን የማግኘት ፍላጎት ቢኖራቸውም መሪዎቹ “በነበረባቸው የስራ ጫና” ምክንያት ሳያገኟቸው ቀርተዋል
ከሰሞኑ በሱዳንና ኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ሰብዓዊነት አሳስቦኝ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ሲሉ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ዲና ሰሞነኛ ጉዳዮችንና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ሳምንታዊ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው ስለ የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ሰሞነኛ ጉብኝት ያነሱት አምባሳደር ዲና ሳማንታ “ሰብዓዊነት አሳስቦኝ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት” ማለታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ሳማንታ “እንደሚወራው መንግስት ለመቀየር አልመጣሁም፤ ይልቁንም ሰብዓዊነት ነው የሚያሳስበኝ” ሲሉ መናገራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ሃገራቸው የተመለሱት የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አግኝቶ የመነጋገር ፍላጎት ነበራቸው፡፡
ይህን ፍላጎታቸውን ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ ለማቅናት ማሰባቸውን ባስታወቁበት ወቅት ገልጸውም ነበረ፡፡
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸው “በነበረባቸው የስራ ጫና” ምክንያት ፍላጎታቸው ተሳክቶ ሳያገኟቸው ቀርተዋል እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፡፡
አምባሳደር ዲና “ነገር ግን ከእርሳቸው ተቋም ተግባር ጋር በሚገናኙ ስራዎች ዙሪያ የተሰማሩ የመንግስት ባለስልጣናትን እንደሚያገኙ ተነግሯቸው፤ የእርዳታ ሃላፊ እንደ መሆናቸው መጠን ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጋር ተወያይተው መንግስት ለምን ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ እንደገባ ገለጻ ተደርጎላቸዋል”ም ብለዋል።
ወ/ሮ ሙፈሪያት ህወሃት የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ ረግጦ መውጣቱን ለሳማንታ መንገራቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡
“አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በጣም ዋጋ ትሰጣለች” ያሉት ሳማንታ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ መድረስ አልነበረበትም ስለማለታቸውም ተናግረዋል፡፡
ድርድርና ውይይትን በተመለከተ በአል ዐይን አማርኛ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና ምናልባትም በመጪው ወርሃ መስከረም መጨረሻ በሚመሰረተው አዲስ መንግስት ሁሉን አቀፍ (All inclusive) ውይይት እንደሚደረግና ምናልባትም የህወሓት አባል የነበሩ ሰዎች ወደዚህ ውይይት ሊመጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።