በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንደገና መጀመሩን መንግስት አስታወቀ
በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ መንግስት አስታውቋል
በሳምንቱ እርዳታ የጫኑ 2 የአውሮፕላን በረራዎችና 83 ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ ገብተዋል
በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰባዓዊ ድጋፍ ከቀናት በፊት እንደገና መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በማህበራዊ ዘፍር የተከናወኑ ስራዎችን ዘስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ክልል የሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች መቀጠላቸውን ገልፀዋል።
በዚህም በትግራይ ክልል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ወደ መቀሌ በአውሮፕላን የሚደረገው ድጋፍ ከቀናት በፊት መጀመሩን አስታውቀዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናትም ሁለት ሰብአዊ ድጋፍን የጫኑ አውሮፕላን በረራዎች ወደ መቀሌ መደረጋቸውንም ሚኒስትር ደኤታዋ ገልፀዋል።
በሰመራ በኩልም አስፈላጊውን ሂደት ያለፉ 83 ምግብ እና ሌሎች እርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ መደረጉንም አስታውቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ በመግለጫቸው አክለውም በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሚሊየን አልፏል ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፤ በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ 265 ሺህ 291 ኩንታል የምግብ እህል እንዲደርስ ተደርጓል ብለዋል።
በአፋር ክልል 76 ሺህ አካባቢ የሚደርሱ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ በዚህም ካለፈው ወር ወዲህ ለእነዚህም ወገኖች ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።