የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትና ተመድ ለትግራይ ክልል የሚሰጡትን የምግብ እርዳታ አቆሙ
ተቋማቱ “ለተቸገሩ ዜጎች የተለገሱ የምግብ እህሎች እየተሰረቁ ለሀገር ውስጥ ገበያ እየተሸጡ ነው” ብለዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የእርዳታ ምግብ ስርቆት የሚያጣራ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) እና ተመድ ለትግራይ ክልል የሚሰጡትን የምግብ እርዳታ ማቆማቸውን ከሰሞኔ አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ይሰጥ የነበረውን የምግብ እርዳታ በጊዜያዊነት ማቆሙን አስታውቋል።
እርምጃው "ከባድ ውሳኔ ነው" ሲሉ የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ተናግረዋል።
ኤጀንሲው በቅርቡ በችግር ውስጥ ላሉ የክልሉ ነዋሪዎች ብሎ የለገሰውን የምግብ እህል ወደ ሌላ ቦታ እየተዘዋወረ ለሀገር ውስጥ ገበያ እየተሸጠ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ጉዳዩ በዋና መስሪያ ቤቱ ቀርቦ ምርመራ የተጀመረ ሲሆን፤ የምግብ እርዳታውን በጊዜያዊነት ለማቆም ከመወሰኑ በፊት ከሰብዓዊ እርዳታ ቢሮው የተውጣጡ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ ተልከዋል ብለዋል።
የአሜሪካ መንግስት ስጋቱን ለኢትዮጵያ መንግስት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ማንሳቱን የጠቀሱት ሰማንታ ፓወር፤ ባለስልጣናቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከአሜሪካ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዩኤስኤአይዲ ጠንካራ የክትትል እርምጃዎች ከተወሰደ በኋላ መርሀ-ግብሩን እንደገና ለማስጀመር ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ሰማንታ ፓወር ችግሩ ሲፈታ እርዳታው ለታለመለት ተጋላጭ ህዝቦች እንደሚደርስ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ባለፈው ሰኞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራምበስርቆት ምክንያት በትግራይ የምግብ እርዳታ ማቆሙን አስታውቋል።
እርምጃውን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ጌታቸው ረዳ ስርቆቱን የሚያጣራ በሌ/ጄነራል ፍሰሃ ኪዳኑ የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቀዋል።
የተመድን ዉሳኔ በችግር ላይ ያለዉን ሰፊ ህዝብ የሚጎዳ ነው ያሉት አስተዳዳሪው፤ ዳግም እንዲጤንም ጠይቀዋል።