የአሜሪካ ግምጃ ቤት በቻይና የመረጃ መንታፊዎች መበርበሩን ገለጸ
በቤጂንግ የሚደገፍ የመረጃ ጠላፊ የሰራተኞች ኮምፒውተሮችና ሚስጢራዊ መረጃዎች ተመልክቷል ተብሏል
በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ግን ውንጀላውን "ምንም ማስረጃ የሌለው ተራ ስም ማጥፋት ነው" ብሎታል
የአሜሪካ ግምጃ ቤት በቻይና የመረጃ መንታፊዎች መበርበሩን ገለጸ።
በቤጂንግ የሚደገፍ የመረጃ ጠላፊ በታህሳስ ወር መጀመሪያ የሰራተኞች ኮምፒውተሮችና ሚስጢራዊ መረጃዎችን መመልከቱን ነው የአሜሪካ ባለስልጣናት የተናገሩት።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ "ትልቅ ክስተት" ነው ያለው ጥቃት ያስከተለውን ጉዳት ከአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና ሌሎች የደህንነት ተቋማት ጋር በመሆን እየመረመረ ነው።
ሚኒስቴሩ ለህግ አውጪዎች የላከው ደብዳቤ መቀመጫውን ቻይና ያደረገ የመረጃ ጠላፊ ለግምጃ ቤቱ ሰራተኞች የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ ሶስተኛ ወገን አገልግሎት አቅራቢ "ሲስተም"ን ጥሶ መግባቱን አመላክቷል።
ሶስተኛ ወገን አገልግሎት አቅራቢው "ቢዮንድ ትሩስት" ከጥቃቱ በኋላ ከአገልግሎት ውጭ (ኦፍላይን) እንዲሆን መደረጉ ተገልጿል።
"ቢዮንድ ትሩስት" ጥቃቱ የደረሰበት በፈረንጆቹ ታህሳስ 2 2024 ነው። ይሁን እንጂ በመረጃ መንታፊዎች እንድተጠለፈ ለማወቅ ሶስት ቀናት ፈጅተውበታል ተብሏል።
ለአሜሪካ ግምጃ ቤት አገልግሎት የሚያቀርበው ድርጅት የተበረበሩት ሚስጢራዊ መረጃዎች ምን አይነት እንደሆኑ ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
የመረጃ መንታፊዎቹ አሁንም የግምጃ ቤቱን መረጃዎች ማግኘት ስለመቀጠላቸው ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት በመረጃ ምንተፋው ዙሪያ በ30 ቀናት ውስጥ ዝርዝር መረጃ ለህግ አውጪዎች እንደሚያቀርብ ገልጿል።
በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃልአቀባይ ሊዩ ፔንግዩ በበኩላቸው ውንጀላው "ምንም ማስረጃ የሌለው ተራ ስም ማጥፋት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አሜሪካ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በቻይና ላይ የምትሰነዝረውን ተደጋጋሚ ውንጀላ ልታቆም ይገባል" ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ድምዳሜ ከመድረስ በፊት በቂ ማስረጃ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አሜሪካ በቻይና የሚደገፉ የመረጃ መንታፊዎች ጥቃት አድርሰውብኛል ስትል የግምጃ ቤቱ የመጀመሪያ አይደለም።
በቅርቡም የቴሌኮም ኩባንያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የግለሰቦች የስልክ ንግግር ቅጂ ተመንትፏል ሲባል የቤጂንግ ስም መነሳቱ ይታወሳል።