በኢሜል ከሚፈጸም የመረጃ ምንተፋ (ፊሺንግ) ራሳችን እንዴት እንጠብቅ?
በኢሜል፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እና በድምጽ አማካኝነት የሰዎችን ሚስጥራዊ ማንነቶች ለመመንተፍ የሚደረገው ሙከራ እየጨመረ ነው
ባለሙያዎቹ ፊሺንግ፣ ስሚሺንግ እና ቪሺንግ የሚሏቸው የመረጃ ስርቆት መፈፀሚያ መንገዶችን አስቀድሞ መለየትና መከላከል ይቻላል
በኢሜል፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እና በቀጥታ ስልክ በመደወል የሚፈጸሙ የማታለልና መረጃ የመመንተፍ ሙከራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ሄደዋል።
በኢሜል በሚላኩ መልዕክቶች ቫይረሶችን ጨምረው በመስደድ የግለሰቦችን መረጃ ለመመንተፍ የሚደረግ ጥረት ፊሺንግ ይባላል።
አጭር የጽሁፍ መልዕክት በሞባይል ስልክ በመላክ የግለሰቦችን ሚስጢራዊ መረጃዎች ለመስረቅ መሞከር ደግሞ ስሚሺንግ ይሰኛል።
የአንድ ተቋም ሃላፊ መስሎ በስልክ በመደወል የተደወለለት ሰው የይለፍ ቃሉን ጨምሮ የተለያዩ ሚስጢራዊ መረጃዎችን እንዲነግራቸው ለማሳመን ጥረት የሚያደርጉበት የማጭበርበር አይነት ደግሞ ቪሺንግ ይባላል።
ሶስቱም የመረጃ መመንተፊያ ዘዴዎች የተለያየ መንገድን ይከተሉ እንጂ የሚያመሳስላቸው ነገር ግን በርካታ ነው።
ቫይረስ የሚላክባቸው የፊሺንግ ኢሜሎችን በትኩረት ከተመለከትናቸው በርካታ አጠራጣሪ ነገር ይታይባቸዋል።
የተቋማት እንዲመስሉ የሚደረጉት ኢሜሎች በጣም ረጅምና ትክክለኝነታቸው አጠራጣሪነትን ማጤን ይገባል።
የሚላኩት መልዕክቶችም የፊደልና የሰዋሰው ችግር ይታይባቸዋል።
የፊሺንግም ሆነ ስሚሺንግ መልዕክቶች የባንኮች፣ ክሬዲት ካርዶች እና ሌሎች አድራሻዎችን የይለፍ ቃል እና ሌሎች ሚስጢራዊ መረጃዎችን እንድናጋራ የሚጠይቁ መሆናቸውም ያመሳስላቸዋል።
መልዕክቶቹ አስቸኳይ እርምጃ እንድንወስድ የሚጠይቁና ስጋታችን ከልክ በላይ የሚያንሩ ሆነው፤ መፍትሄውም ይህንን ሊንክ ተከትላችሁ እንዲህ ስታደርጉ ነው ይላሉ።
የሳይበር ጥቃት ፈፃሚዎች የሰው ልጆች የሚጋሯቸውን ባህሪያት በማጥናት ለያዙት አላማ ይጠቀሙባቸዋል።
የሰው ልጅ በፍርሃት ሲርድና አጣዳፊ ነገር ሲገጥመው የማስተዋያ አቅሉን እንደሚያጣ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ስጋት ይልኩለታል፤ መፍትሄውንም ይሄው በማለት የክፉ ጊዜ ደራሽ መስለው ይከሰታሉ። የተጨነቀው ሰውም አድርግ ያሉትን ሁሉ ለመፈፀም ስለማያንገራግር ኢላማቸውን ያሳካሉ።
የፊሺንግ፣ ስሚሺንግ እና ቪሽንግ የማጭበርበሪያ መልዕክቶችን የሚልኩ ሰዎች ባልቆረጥነው ሎተሪ ጃክፖት ተሸላሚ አድርገውን ቁጭ ሊሉ ይችላሉ። የበርካታ ሰዎችን ጉጉትና ስስት ያውቃሉና በደካማ ጎናቸው ገብተው መጠቀሙንም ተክነውበታል።
እናም በአጉል ምኞት ሰክረን ያዘዙንን ከመፈጸም መቆጠብ ይገባል ነው የሚሉት ባለሙያዎች።
ከማናውቀው ሰው የተለከ መልዕክትና ተያይዞ የተላከን ሊንክ ባለመክፈም የፊሺንግ እና ስሚሺንግ ጥቃትን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ያሳስባሉ።
በስልክ ደውለው የይለፍ ቃል እና ተያያዥ መረጃዎችን የሚጠይቁ ሰዎችንም በጥንቃቄ ማድመጥ፤ በአካል እመጣለሁ ማለትና ምንም አይነት ሚስጢራዊ ከመስጠት መቆጠብ እንዳለብን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው፥ በፊሺንግ የሚፈጸም የመረጃ ምንተፋ በመረጃ ዘራፊዎች ከሚፈጸሙ ማጭበርበሮች አራተኛውን ደረጃ ይዟል።
በ2021 ብቻም በዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑ የቢዝነስ ተቋማት በአማካይ የ4 ነጥብ 65 ሚሊየን ዶላር ካሳ ለዘራፊዎቹ መክፈላቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያም የኤሌክትሮኒክ ንግድ ስርአት እየጨመረ በመሄዱ የፊሺንግ፣ ስሚሺንግ እና ቪሺንግ ጥቃቶችን መመከቻ መንገዶችን አስቀድሞ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው።