አሜሪካ፣ ካናዳ እና ብሪታንያ ኢትዮጵያ የቬና ዲፕሎማቲክ ስምምነት መጣሷ እንዳሳሰባቸው ገለጹ
በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ሰራተኞች ላይ የደረሰው እንግልት እንዳሳሰባቸው ኢምባሲዎቹ አስታውቀዋል
የአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲስ አበባ ቢሮውን እንደሚዘጋ መግለጹ ይታወሳል
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ብሪታንያ ኢትዮጵያ የቬና ስምምነት መጣሷ እንዳሳሰባቸው ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ያሉ ሁለት የባንኩ ሰራተኞች በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች ድብደባ፣ እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር።
ባንኩ እንዳለው ሁለት ሰራተኞቹ የቬና የዲልሎማሲ ጥበቃ ስምምነትን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሮ አስተናጋጅ ሀገራት ስምምነትን የጣሰ ክስተት በኢትዮጵያ መፈጸሙንም ገልጿል።
የተፈጠረውን ክስተት ለኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ማመልከቱን የሚገልጸው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጉዳዩ መፈጸም እንደሌለበት፣ ህግ መጣሱን እና ጉዳዩ ተመርምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ በኢትዮጵያ በኩል ቃል ተገብቶልኛል ሲልም በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡
ባንኩ አሁን ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል በገባው መሰረት በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዳልወሰደ እና ጉዳዩን ስለመመርመሩ መረጃ እንዳልሰጠው ገልጿል፡፡
የአሜሪካ፣ ካናዳ እና ብሪታኒያ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጥበቃ ለማድረግ የገባችውን የቪየና ስምምነት መጣሷ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮውን ሊዘጋ እንደሚችል አስጠነቀቀ
ሀገራቱ ባወጡት መግለጫ የቪየና ስምምነት መጠበቅ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች በነጻነት ስራቸውን እንዲሰሩ የሚያደርግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የካናዳ ኢምባሲ በቀድሞው ትዊትር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መግለጫ እንዳሉት በአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ላይ እንግልት የፈጸሙ አካላት እስካሁን አለመጠየቃቸው እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡
ብሪታንያ በበኩሏ ለመላው አፍሪካ እና ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፈንድ እንደምታደርግ ገልጻ በኢትዮጵያ በኩል በባንኩ ሰራተኞች ላይ የተፈጸመው ክስተት ተቀባይነት እንደሌለው እና ተጠያቂነት እንዲኖር አሳስባለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ "ከአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ቢሮ ጋር የተፈጠረው ክስተት ባንኩ ቢሮውን እንዲዘጋ አላደረገውም፣ የሁለቱ ግንኙነትም አልተቋረጠም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ይሁንና የኢትዮጵያ ጸጥታ ሀይሎች በአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲስ አበባ ቢሮ ሰራተኞች ላይ ለምን ድብደባ እንደፈጸሙ ከሁለቱም ወገኖች በኩል በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።