የጸጥታው ምክርቤት የተኩስ አቁም ውሳኔ ሀሳብ አሜሪካ በመቃወሟ ሳይጸድቅ ቀረ
እስራኤል እና ሀማስ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የተቃወመችው አሜሪካ ለአጋሯ እስራኤል ከላለ ሆናለች
15 አባላት ካሉት ጸጥታው ምክርቤት ውስጥ 13 በአረብ ኢምሬትስ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የደገፉት ሲሆን ብሪታኒያ ድምጽ ከመስጠት ታቅባለች
የጸጥታው ምክርቤት የተኩስ አቁም ውሳኔ ሀሳብ አሜሪካ በመቃወሟ ሳይጸድቅ ቀረ።
የተመድ የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር(ቬቶ) የማድረግ መብቷን ተጠቅማ እንዳይጸድቅ ማድረጓን ሮይተረስ ዘግቧል።
እስራኤል እና ሀማስ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የተቃወመችው አሜሪካ ለአጋሯ እስራኤል ከላለ ሆናለች።
15 አባላት ካሉት ጸጥታው ምክርቤት ውስጥ 13 በአረብ ኢምሬትስ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የደገፉት ሲሆን ብሪታኒያ ድምጽ ከመስጠት መታቀቧ ተገልጿል።
ይህ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበው የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሁለት ወር ያስቆጠረው የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት አለምአቀፍ ቀውስ ደቅኗል ሲሉ የጸጥታው ምክርቤትን ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
"የማያቋርጠው የጋዛ ድብደባ እንዲቆም ካልተባበርን፣ ለፍልስጤማውያን የምናስተላልፈው መልእክት ምንድነው?" ሲሉ በተመድ የአረብ ኢምሬትስ አምባሳደር መሀመድ አቡሻሀብ ምክርብቱን ጠይቀዋል።
"በርግጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ በሌላ የአለም ክፍል ላሉ ንጹሃን የምናስተላልፈው መልእክትስ ምን ነው?" ሲሉ ጥያቄ አስከትለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ተኩስ አቁሙን የሚቃወሙት የሚጠቅመው ሀማሰን ብቻ ነው በሚል ምክንያት ነው።
አሜሪካ ጦርነቱ ጋብ ብሎ ንጹሃን ከጥቃት የሚጠበቁበት መንገድ እንዲመቻች እና ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ባደረሰው ጥቃት ያገታቸው እስራኤላውያን እንዲለቀቁ ትፈልጋለች።
በኳታር አደራዳሪነት ጦርነቱን ጋብ የማድረግ ስምምነት መጣሱን ተከትሎ እየተደረገ ያለው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል።
የእስራኤል እግረኛ ጦር በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ትልቋ ከተማ ካን ዮኒስ ውጊያ እያካሄደ ነው።
ጦርነቱን እንዲቆም የተደረጉ አለምአቀፍ ጫናዎች ለውጥ አላመጡም።