እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ጥቃት ንጹሃንን መጠበቅ አልቻለም - ብሊንከን
ሁለተኛ ወሩን በያዘው ጦርነት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ17 ሺህ በላይ ደርሷል
የጸጥታው ምክርቤት በኤምሬትስ በቀረበው የሰብአዊ ተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ ላይ ዛሬ ድምጽ ይሰጣል
የእስራኤል መንግስት ወደ ጋዛ ሲዘልቅ የገባው ቃል እና በንጹሃን ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ሰፊ ልዩነት እንዳለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።
ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ከብሪታንያ አቻቸው ዴቪድ ካሜሮን ጋር ከመከሩ በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ እስራኤል ፍልስጤማውያን ንጹሃን ላይ ያደረሰችውን ጉዳት ተቃውመዋል።
“እስራኤል ንጹሃንን ለመጠበቅ ቃል ብትገባም መሬት ላይ የምናየው በተቃራኒው ነው” ብለዋል ብሊንከን።
ሃማስን ሙሉ በሙሉ እደመስሳለሁ በሚል ወደ ጋዛ ጦሯን ያስገባችው ቴል አቪቭ ፍልስጤማውያን ከጦርነቱ ቀጠና እንዲወጡ ብታዝም በተፈናቀሉበትም ጥቃት ማድረሷን ገፍታበታለች።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ሁለተኛ ወሩን በያዘው ጦርነት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 17 ሺህ 170 ደርሷል፤ ከ46 ሺህ በላይ ሰዎችም ቆስለዋል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሶስት ጊዜ ቴል አቪቭን የጎበኙት ብሊንከን የእስራኤልን ንጹሃንን ያለመጠበቅ ችግር አጥብቀው መቃወማቸው ቢገለጽም ሀገራቸው በጋዛ ጦርነቱ እንዲቀጥል መፈለጓን በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በትናንትናው እለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ ጋር በስልክ ሲወያዩ የፍልስጤማውያን ንጹሃን ጉዳይ ትኩረት የሚሻው መሆኑን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ በርግጥም በጋዛ የፍልስጤማውያን ሰቆቃ እንዲቆም ከፈለገች ግን በዛሬው እለት በጸጥታው ምክር ቤት ለሚቀርበው የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ ድጋፏን ማሳየት እንዳለባት ተንታኞች ያነሳሉ።
በአረብ ኤምሬትስ የሚቀርበው የውሳኔ ሃሳብ በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲደርስ እና በሃማስ የታገቱ እስራኤላውያን እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ነው።
ይህ የውሳኔ ሃሳብ የሚጸድቀው ግን ከ15ቱ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ዘጠኙ ከደገፉትና አሜሪካን ጨምሮ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስት ሀገራት ሳይቃወሙት ከቀሩ ብቻ ነው።
እንደ እስራኤል ሁሉ የተኩስ አቁም ውሳኔው የሚጠቅመው ሃማስን ብቻ ነው የሚል እምነት የነበራት አሜሪካ በዛሬው የጸጥታው ምክርቤት የምታሳልፈው ውሳኔ ይጠበቃል።
ኤምሬትስ እና ግብጽን ጨምሮ በርካታ የአረብና ሙስሊም ሀገራት ግን በጋዛ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳቡ እንዲጸድቅ ግፊት እያደረጉ ነው።