አሜሪካና አጋሮቿ ሱዳን ቀውሷን ለመፍታት አዲስ ስምምነት መፈረሟን እንቀበላለን አሉ
የሱዳን ኃይሎች የሽግግር ሲቪል መንግስት ለማቋቋም ያለመ የመጀመሪያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል
ስምምነቱ ከአንዳንድ የሲቪል ቡድኖች ቁጣ እንደገጠመው ተነግሯል
አሜሪካ እና አጋሮቿ ባለፈው ዓመት በመፈንቅለ መንግስት የተቀሰቀሰውን የፖለቲካ ቀውስ ለማስቆም በሱዳን ወታደራዊ እና ሲቪል መሪዎች መካከል ስምምነት መፈረሙን በበጎ እንቀበላለን አሉ።
ከሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኤምሬትስ እና ብሪታንያ "የመጀመሪያውን የፖለቲካ ማዕቀፍ ስምምነት በደስታ ተቀብለዋል" ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በጋራ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ሱዳን በፈረንጆቹ በጥቅምት 2021 የጦሩ አዛዡ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ በተቃውሞ እና በምጣኔ-ሀብት ውጣ ውረድ ስግ ተይዛለች። ይህም አንጋፋው መሪ ኦማር አል በሽርን ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የተጀመረውን የሲቪል አገዛዝ ሽግግር ማደናቀፉን ጋርዲያን አጃንስ ፍራንስ ፕረስን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሰኞ እለት ቡርሃን፣ የፓራሚታሪ አዛዥ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ እና በርካታ የሲቪል ቡድኖች፣ በመፈንቅለ መንግስቱ ከስልጣን የተባረረው ዋና የሲቪል ቡድን በተለይም የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች የሽግግር ሲቪል መንግስት ለማቋቋም ያለመ የመጀመሪያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
አጋሮቹ በመግለጫቸው ስምምነቱን “በሲቪል የሚመራ መንግስት ለመመስረት እና ህገ-መንግስታዊ ዝግጅቶችን ለመወሰን ሱዳንን ወደ ምርጫ ለሚወስድ የሽግግር ጊዜ አስፈላጊ የመጀመሪያ እርምጃ ነው” ሲሉ አወድሰዋል።
ስምምነቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት፣የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች እንዲሁም የሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለስልጣናት በተገኙበት መደረጉን አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ የሲቪል ቡድኖች ከጦሩ ጋር የተደረገውን ድርድር ውድቅ በማድረግ ስምምነቱን እንደ ክህደት በመቁጠር ቁጣ ተነስቷል ነው የተባለው።
የጋራ መግለጫው “ሁሉም የሱዳን ተዋናዮች በዚህ ድርድር ላይ በአስቸኳይ እና በቅን ልቦና እንዲሳተፉ እናሳስባለን” ብለዋል።
ሁሉም ወገኖች የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም “ከጠባብ የፖለቲካ ዓላማዎች” በላይ እንዲያስቀድሙም ሀገራቱ ጥሪ አቅርበዋል።