ግጭቱ የተከሰተው በሱዳን ነጻ አውጪ አማጺ ቡድኖች አባላት መካከል ነው ተብሏል
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ዳግም ግጭት ማገርሸቱ ተገለጸ፡፡
በጎረቤት ሀገር ሱዳን ዳርፉር ግዛት በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የ13 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ስድስት ሰዎች ተጠልፈው ያሉበት የማይታወቅ ሲሆን አራት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም 12 ሰዎች ደግሞ እስካሁን በግጭቱ ይሙቱ ወይም በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ እንደማይታወቅ የተገለጸ ሲሆን ግጭቱ ሊቀጥል እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡
የምዕራብ ሱዳን አካል የሆነው ዳርፉር ግዛት በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትበት ሲሆን ከትናንት በስቲያ በማዕከላዊ ዳርፉር ልዩ ቦታው ኡሙ እና አርሽን በሚባሉ ቦታዎች አዲስ ግጭት መፈጠሩ ተገልጿል፡፡
ተመድ በሪፖርቱ እንዳሳወቀው ግጭቱ የተቀሰቀሰው በሱዳን ነጻ አውጪ አማጺ ቡድን እና ከዚህ ቡድን ተከፍለው በወጡ አባላት መካከል ነው፡፡
ግጭቱ በመስፋፋት ላይ እንደሆነ የገለጸው ተመድ በተለይም ዳያ፣ ዋራ እና ኪያ በተባሉ መንደሮች ተስፋፍቷል የተባለ ሲሆን በዚህ ግጭት ምክንያት እስካሁን ከ5 ሺህ 600 በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም ገልጿል፡፡
ተፋላሚ ወገኖች ዳግም ለመዋጋት ሀይል እያሰባሰቡ መሆኑን መረጃ እንዳለው የሚገልጸው ይሄው ተቋም ግጭቱ እንዲቆም እና የሚመለከታቸው ሁሉ ጫና እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ 13 ሰዎች ሲሞቱ 15 ሰዎች ደግሞ ቆስለው እንደነበር በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የሱዳን ነጻ አውጪ አማጺ ቡድን ወይም በምህጻረ ቃሉ “ኑር” በመባል የሚጠራ ሲሆን በፈረንጆቹ 2020 በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ካልፈረሙ አማጺ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዚህ አማጺ ቡድን አባላት መካከል መከፋፈል የተከሰተ ሲሆን ይህ መከፋፈል ወደ ማህበረሰቡ ወርዶ ለንጹሃን መሞት ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል፡፡