ኢትዮጵያ እና ሱዳን የጋራ ድንበራቸውን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት መስማማታቸው ተገለጸ
አቶ ደመቀ መኮንን ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ፕሬዝዳን ሌ/ጄ አልቡርሃንና ም/ሊቀመንበር ሀምዳን ዳጋሎ ጋር መክረዋል
ሁለቱ ሀገራት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለባቸውን ልዩነትም በውይይት ለመፍታት መስማማታቸው ተገልጿል
ኢትዮጵያ እና ሱዳን የጋራ ድንበራቸውን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት መስማማታቸው ተገለጸ።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ወይም ኢጋድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ በሱዳን መዲና ካርቱም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ከምክትላቸው ሀምዳን ዳጋሎ ጋር በካርቱም መወያየታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ሁለቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን በሰላም ለመፍታት የተስማሙ ሲሆን በተለይም ሁለቱ ሀገራት በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በኢትዮ ሱዳን ድንበር ላይ ያለባቸውን ልዩነቶች በሰላም ለመፍታት መስማማታቸው ተገልጿል
በካርቱም የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ለሱዳን ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሁለቱ ሀገራት በሚያቋቁሟቸው የጋራ መንገዶች ልዩነቶቻቸውን በሰላም ለመፍታት ወስነዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች የሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ትብብሮች ዙሪያ እንደተወያዩ ተገልጿል።
በፌደራል መንግስት እና ህወሃት መካከል የተካሄደው የሰላም ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን ሱዳን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች ጄነራል አልቡርሃን መናገራቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል አልቡርሃን የወቅቱ የኢጋድ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።