አሜሪካ ኡሁሩ ኬንያታ “የኢትዮጵያና የዲ.አር.ሲ የሰላም መልዕክተኛ” ሆነው መሾማቸውን እንደምትቀበል ገለጸች
ኡሁሩ ኬንያታ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል
አሜሪካ ተለዋዋጭ ሁነታዎች በሚስተዋሉበት ቀጠና “ኬንያታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ አለን” ብላለች
አሜሪካ ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም መልዕክተኛ ሆነው መሾም በደስታ እንደምትቀበል ገለጸች፡፡
የአሜሪካ መንግስት በውጭ ጉዳይ መሰሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በኩል ባወጣው መግለጫ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የአፍሪካ ቀንድ እና የታላላቅ ሀይቆች አካባቢ የሰላም መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውን በደስታ እንደሚቀበል አስታውቋል።
ቢሮው ተለዋዋጭ ሁነታዎች በሚስተዋሉበት ቀጠና ኬንያታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ አለን ብሏል፡፡
“ኡሁሩ ኬንያታ በሰሜን ኢትዮጵያ እና በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለተፈጠረው ግጭት የሰላም መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውን በደስታ እንቀበላለን፤ ኬንያታ በዚህ ጊዜ ሁለቱም ግጭቶች ለመፍታት የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ይሆናል" ብሏል ቢሮው በትዊተር ገጹ ላይ ባጋራው ጽሁፍ፡፡
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቀናት በፊት በነበረው በዓለ ሲመታቸው በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያከናውኑትን ተግባር እንደሚቀጥሉ መናጋራቸው ይታወሳል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ተዋጊ ኃይሎችን ከማደራደር ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ የኡሁሩ ኬንያታ ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
በተለይም አሁን ላይ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለመሰደራደር ዝግጁ መሆናቸው የሚገልጹት የትግራይ ኃይሎች፤ ከመንግስት ጋር በሚደረገው ድርድር ከአፍሪካ ህብረት ይልቅ በቅርቡ ስልጣናቸውን ያስረከቡት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያሸማግሏቸው በተደጋጋሚ በይፋ ጠይቀው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ለሚካሄደው ጦርነት መፍትሔ በመፈለጉ በኩል የአፍሪካ ህብረት ቀዳሚው አሸማጋይ ሊሆን እንደሚገባ ቀደም ሲል በያዘው አቋም እንደጸና መሆኑ ይታወሳል።