መንግስት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ አስተጓጉሏል ሲል ህወሓትን ከሰሰ
ግጭት ከማቆም ውሳኔው በኋለ ህወሓት እርዳታ ወደ ትግራይ አልደረሰም ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ሲል ግጭት ካቆመ በኋላ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረው የእርዳታ በረራ በየቀኑ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል
የኢትዮጵያ መንግስት ህወሓት በየብስ በኩል ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የማድረስ እንቅስቃሴን ማስተጓጎሉን አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው መግለጫ የህወሓት ታጣቂዎች የአብአላ መንገድን በመዝጋታቸው ምክንያት በአለም የምግብ ድርጅት እንዲያጓጓዝ የተፈቀደው በ43 መኪና የተጫነ የርዳታ እህል ወደ ትግራይ ማጓጓዝ አለመቻሉን ገልጿል፡፡
ህወሓት በበኩሉ መንግስት የሚያቀርበውን ክስ አይቀበልም፡፡
ህወሓት የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም ካደረገበት መጋቢት 15 ጀምሮ ባሉት አራት ቀናት ውስጥ ምንም አይነት ሰብአዊ ድጋፍ አልገባም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ሲል ግጭት ካቆመበት ቀን ጀምሮ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረው በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ለአለም አቀፍ የእርዳታ ሰጭ ተቋማት ፍቃድ መስጠቱን ገልጿል፡፡
መንግስት በትግራይ ያሉ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ ቢጥርም በሌላኛው ወገን(ህወሓት) በኩል ትብብር እንደሌላ አስታውቋል፡፡
የሰብአዊ እርዳታ ለማረስ ቀርጠኛ መሆኑን የገለጸው መንግስት የህወሓት ታጣዊዎች ምክንያት ከመደርደርና የተዛባ መረጃ ከማሰራጨት ተቆጥበው የእርዳታ እህሉ እንዲደርስ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
መንግስት የህወሓት ታጣቂዎች በጉልበት ከያዟቸው የአፋር እና አማራ ክልሎች እንዲወጡ አለም አቀፍ ተቋማት ጫና ማሳደር አአለባቸው ብሏል፡፡
አንድ አመት ከሰባት ወር የሞላው በኢትዮጵያ ተቀሰቀሰው ግጭት፤ በሰላም እንዲፈታ አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት ጥረቶች ጀምረዋል፡፡
በግጭቱ በትግራይ፣በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው በመፈናቀል ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ሆኗል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንደሚከተል አስታውቆ ነበር፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ለማስቻል የተኩስ አቁም ማወጁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የመንግስትን መግለጫ ተከትሎ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ወደ ትግራይ የሚገባበት ሁኔታ ከተፈጠረ ተኩስ ለማቆም ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡