አሜሪካ በኢትዮጵያ ዳግም ግጭት መጀመሩ እንደሚያሳስባት ገለጸች
“ዳግም ወደ ግጭት መግባት የሰዎችን ስቃይ፣የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና ተጨማሪ አኮኖሚያዊ ችግሮች ያስከትላል” ብላለች አሜሪካ
አንቶኒ ብሊንከን ፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ቁርጠኛ አቋም እንዳለትም አረጋግጠዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፤ በኢትዮጵያ ዳግም ግጭት መጀመሩ አሜሪካን እንደሚያሳስባት ገልጸዋል፡፡
ብሊንከን ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲሁም በመጨረሻም ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት በኢትዮጵያ መንግስት የታወጀው እና ህወሓት የተቀበለው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ፣ በአፋር እና አማራ ክልሎች በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ መቻሉ ተችሎ ነበር ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በቅርብ ጊዜ የተቀሰቀው ጦርነት፣ ትንኮሳ የተሞላባቸው ትርክቶችና እንዲሁም ዘላቂ የተኩስ አቁም እጦት እየታዬ የነበረውን መሻሻል አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዳግም የተቀሰቀሰው ግጭት ለጋራ ደህንነት እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ብልጽግናና እድገት እውን ለማድረግ የሚደረገውን ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደትና ጥረት የሚያዘገይ ነው ብለዋል አንቶኒ ብሊንከን፡፡
አንቶኒ ብሊንከን በዚህ መግለጫቸው የኢትዮጵያ መንግስት ተደራዳሪ ቡድን ማቋቋሙን እና ለሰላም ውይይት ያለውን ፍላጎት መግለጹን እንገነዘባለን ብለዋል።
ሁሉም ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ምግብ እና የነዳጅ አቅርቦትን እንዲያስቀጥሉ፣ ከወታደራዊ ኃይል እንዲታቀቡ እና መስረታዊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጠይቀዋል አንቶኒ ብሊንከን።
“አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ እንዲሁም በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ቁርጠኛ አቋም አላት፡፡ ሀገሪቱ ያጋጠሟትን እንደ ድርቅ መቋቋምን እና ቀጠናዊ ደህንነትን ማስፈንን የመሳሰሉ ሁለንተናዊ ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ በምታደርገው ጥረት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን" ሲለም ተናግረዋል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን በትናንትነው እለት ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ህወሓት እሮብ እለት ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል፡፡
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተለያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡